ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እንስሳት እርባታ ባለሙያዎች ማህበር ጉባኤ በባህር ዳር በመካሄድ ላይ ነው

ባህር ዳር ነሀሴ 17/2010 አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ በመደረግ ላይ ባለው ጥረት የእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፉ የሚያበረክተውን ድርሻ ለማሳደግ  እየተሰራ መሆኑን የግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስቴር አስታወቀ። የኢትዮጵያ እንስሳት እርባታ ባለሙያዎች ማህበር ''የእንስሳት ዘርፍን ወደ ላቀ ውጤታማነት ማሸጋገር'' በሚል መሪ ቃል 26ኛውን ዓመታዊ ጉባኤ በባህር ዳር እያካሄደ ነው። ሚኒስትር ዲኤታው ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንዳሉት የእንስሳት ሃብት ልማትን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን በማጸደቅ ተግባራዊ እንዲሆኑ ተደርጓል። በተለይም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን መርሃ ግብር የእንስሳት ልማት ዘርፉን ለመለወጥ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል። የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል፣ የምርት ጥራት ማሳደግ፣ የውጭና የአገር ውስጥ የገበያ ትስስር መፍጠር፣ በቴክኖሎጅ አቅርቦት፣ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል። በዚህም የእንስሳት ባለሙያዎችን እስከ ቀበሌ ድረስ መመደብ፣ ልማቱ በእውቀትና ክህሎት የዳበሩ እንዲሆን ተከታታይ ስልጠናና የልምድ ልውውጥ እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ የግብዓት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ጥረት ተደርጓል። እየተከናወኑ ያሉት ተግባራትም ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ ለሚደረገው ጥረት የእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፉ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁን እየተካሄደ የሚገኘው የእንስሳት ሃብት ባለሙያዎች ማህበር ዓመታዊ ጉባኤም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማንሳት ለፖሊሲ አውጭዎችና ለአጋር አካላት ግብዓት የሚቀርብበት መድረክ እንደሚሆን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የእንስሳት ሃብት ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ጌታቸው ብሩ በበኩላቸው ማህበራቸው በእንስሳት ልማት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርበው እየሰሩ ነው። በዚህም ጥናትና ምርምር በማድረግ፣ የዘርፉን ባለሙያዎች አቅም በመገንባት፣ ለዘርፉ እድገት ጠቃሚ የሆኑ ፖሊሲዎች እንዲወጡና አዳዲስ ቴክኖሎጅዎች እንዲተዋወቁ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው። በቅርቡም ማህበሩ በአገር አቀፍ ደረጃ የእንስሳት ማዳቀል ፖሊሲና የእንስሳት ልማት ፍኖተ ካርታ እንዲጸድቅ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ሌሎች አገራት ተሞክሮ እንዲወስዱ ማስቻሉን ተናግረዋል። በክልሉ በእንስሳት ሃብት ምርምር በማድረግ በዝርያ ማሻሻልና ምርት ማሳደግ የሚሰሩ ሰባት የምርምር ማዕከላት መኖራቸውን የጠቁሙት ደግሞ በአማራ ግብርና ምርምር ተቋም የእንስሳት ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ሊቃውንት ይሄይስ ናቸው። የምርምር ማዕከላቱም የእንስሳት ዝርያ በማሻሻል፣ የወተትና ስጋ ምርት በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ተቋማቸው ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን ተናግረዋል። በባህርዳር ከተማ ዛሬ የተጀመረው ዓመታዊ ጉባኤ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በሚቀርቡ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ መግባባት ላይ በመድረስ ለህትመትና ለባለድርሻ አካላት እንደሚቀርብ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም