ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በጊዜያዊነት የሚመደቡ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጁ ሆኗል

95

አዲስ አበባ ፣ህዳር 24/2014(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት ጦርነት በከፈተባቸው አካባቢዎች ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች በጊዜያዊነት የሚመደቡ ተማሪዎችን ለመቀበል መዘጋጀቱን የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

በትግራይ ክልል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎችና በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ የነበሩ መደበኛ ተማሪዎች ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የሚመደቡ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ባለፈው ጥቅምት ወር መግለጹ ይታወሳል።

አሸባሪው ህወሃት በአማራ እና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ወረራ በመፈፀም ግልፅ ጦርነት የከፈተ ሲሆን ዘረፋና ውድመት አስከትሏል።

በእነዚህ አካባቢዎች በተለይም የትምህርትና የጤና ተቋማትን በተደራጀ መልኩ በመዝረፍ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱም ይታወቃል።

ችግሩን ተከትሎ ትምህርት ሚኒስቴር በትግራይ ክልል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎችና በአማራ ክልል ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በጊዜያዊነት ተመድበው እንዲማሩ ወስኗል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፤ ትላንት በሰጡት መግለጫ አሸባሪው ህወሃት ጦርነት በከፈተባቸው አካባቢዎች ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች በጊዜያዊነት ወደ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ይመደባሉ ብለዋል።

በዚሁ መሰረትም የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በጊዜያዊነት ለመቀበል መዘጋጀቱን ገልጿል።

በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ከለለው አዲሱ፤ ዩኒቨርሲቲው በጊዜያዊነት ተመድበው የሚመጡ ተማሪዎችን ለመቀበል አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም