የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማጥፋት የህጎች ተፈጻሚነት ላይ ማተኮር ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማጥፋት የህጎች ተፈጻሚነት ላይ ማተኮር ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ ነሀሴ 17/2010 በኢትዮጵያ ያለዕድሜ ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት እንዲቻል ተግባራቱን ለመከላከል የወጡ ህጎችን በማስፈፀም ረገድ በትኩረት መስራት ይገባል ተባለ። ኢትዮጵያ የዛሬ አራት ዓመት በእንግሊዝ ለንደን በተካሄደው የዓለም ታዳጊ ሴቶች ጉባኤ ላይ ያለዕድሜ ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን እስከ 2017 ድረስ ለማስቆም ቃል ገብታ ነበር። የኢትዮጵያ ህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሜሮን አራጋው ከሶስት ዓመት በፊት በነበረው ሁኔታ ከሴት ልጅ ጠለፋ፣ ግርዛት፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ ለማህበሩ የሚቀርቡ ቅሬታዎች ቀንሰው እንደነበር ያስታውሳሉ። በተለይ ካለፉት ሶሰት ዓመታት ወዲህ ግን እነዚህ ጥቃቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን የሚያመላክቱ ጥቆማዎች መኖራቸውን አስተውያለሁ ይላሉ። እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ አዲስ አበባን ጨምሮ የሚመሩት ማህበር በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ያለድሜ ጋብቻ፤ በሌሎች ክልሎች ደግሞ ግርዛት፣ ጠለፋና መሰል ሴት ልጅ ላይ የሚፈፀም ጥቃት እያገረሸ መጥቷል። ዳይሬክተሯ በሴት ልጆች ላይ የሚፈፀመው ጥቃት እየጨመረ ሊመጣ የቻለበት አንዱ ምክንያት ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ጋር ተያይዞ በሴቶች መብት ላይ የሚሰሩ ሲቪክ ማህበራት ግንዛቤ በመፍጠርና ህጎችን ለማስፈጸም የሚከናወነው ተግባር በመቀዛቀዙ ነው ይላሉ። በመሆኑም ኢትዮጵያ በ2017 ዓም የሴት ልጅ ያለ እድሜ ጋብቻንና ግርዛትን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የገባችውን ቃል ኪዳን እውን ማድረግ ይቻላት ዘንድ የተቀዛቀዘውን ስራ ማጠናከር የግድ ይላል ባይ ናቸው። በዚህም የሴት ልጆች መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ የወጡ ህጎች ተፈጻሚነት ላይ ጠንካራ የክትትል ሥራ እንደሚያስፈልግ ወይዘሮ ሜሮን አሳስበዋል። በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት ትኩረት አድርጎ የሚሰራውና "ኬኤምጂ ኢትዮጵያ" የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ቦጋለች ገብሬ ድርጊቱን ለማስቆም ከሴቶች ከራሳቸው ጀምሮ ቅንጅታዊ አሰራር ያስፈልጋል ይላሉ። ድርጅታቸው በሚሰራባቸው ደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በተለይም ከንባታ አካባቢ የሴት ልጅ ግርዛት መቀነሱን ነው የሚናገሩት። ዶክተር ቦጋለች እንደሚሉት ድርጅታቸው በሚሰራበት አካባቢ ለውጦች ይታዩ እንጂ በሌሎች አካባቢዎች ሴቶች አሁንም የተለያዩ ጥቃቶች ሰለባ ናቸው። በመሆኑም በ2017 ግርዛትንና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረትና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመቀነስ የተቀናጀ ስርዓት የተበጀለት አሰራር ያስፈልጋል ብለዋል። በ2016 ይፋ በሆነው የስነ-ህዝብና ጤና ጥናት መሰረት በኢትዮጵያ 65 በመቶ በሚሆኑ ሴት ልጆች ላይ ግርዛት ይፈፀማል። የሴቶች አማካይ የመጀመሪያ የጋብቻ ዕድሜ ክልል ደግሞ 17 ዓመት መሆኑን ጥናቱ ያሳያል። የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ጸጋዬ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመቀነስ እየተሰራ ቢሆንም ተግባሩ አሁንም ከፍተኛ መሆኑን ያምናሉ። ኢትዮጵያ የገባችውን ቃልኪዳን ለማሳካት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን እንዲህ ያብራራሉ። ትብብርን በማጠናከር የሚመለከታቸውን አካላትን ያቀፈ ያለዕድሜ ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን የማስቆም ብሔራዊ ጥምረት ተቋቁሞ እንቀስቃሴ ተጀምሯል። ጠንካራ የሕግ አፈፃፀምና የተጠያቂነት አሰራርን ለመዘርጋት እንዲቻልም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን የማስወገድ ስትራቴጂና መርሃ-ግብርን መሰረት ያደረገ የአምስት ዓመት አገራዊ ፍኖተ-ካርታ ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጅቷል። የሚመለከታቸው አካላት ከመከሩበት በኋላ ይጸድቃል የተባለው ፍኖተ-ካርታ የሴት ልጅን ያለዕድሜ ጋብቻና ግርዛት ለማስቆም የሚያስፈልጉ ግብአቶችን፣ መከናወን ያለባቸው ተግባራት፣ እንዴትና በማን እንደሚከናወኑ አቅጣጫ የሚያመላክት ነው።