በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ተጠግነው ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተሰራ ነው

98

ባህርዳር፣ ህዳር 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን 34 የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት መልሶ በመጠገን ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።

ቡድኑ በወረራ በያዛቸው የክልሉ አካባቢዎችም ከ520 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው 103 የንፁህ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተመላክቷል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ማማሩ አያሌው ዛሬ በሰጡት መግለጫ አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በቆየባቸውና ተሸንፎ በወጣባቸው የተለያዩ ዞኖች ያወደማቸውን የውሃ ተቋማት መልሶ የመጠገን ሥራ እየተከናወነ ነው።

ኃላፊ እንዳሉት፤ ተጠግነው ለአገልግሎት የበቁት የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት በዛሪማ፣ ደብረዘቢጥ፣ ፍላቂት፣ ጋህሳይ፣ በንፋስ መውጫና በሌሎች መካከለኛና አነስተኛ የገጠር ከተሞች ጭምር የሚገኙ ናቸው።

ለውሃ ተቋማቱ 120 የተለያየ መጠን ያላቸው የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከሮች፣ 16 ጄኔሬተሮች እና ስምንት ፓምፖችን የመትከልና የመጠገን ሥራ ተከናውኗል።

ለውሃ ተቋማቱ የጥገና ሥራ ከፌዴራልና ከክልሉ መንግስት፣ እንዲሁም ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የተገኘ 70 ሚሊዮን ብር ወጭ መደረጉንም የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።

ከቄዬአቸው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ወገኖች ተንቀሳቃሽ የውሃ ታንከሮችን በመትከል በውሃ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ንፁህ ውሃ እንዲቀርብ እየተደረገ እንደሆነም አመልክተዋል።

በግንባር ጠላትን እየተፋለመ ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖም የውሃ አቅርቦቱ በስፋት መከናወኑን ነው ያስረዱት።

በክልሉ በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰባቸውን የመጠጥ ውሃ ተቋማት ጠግኖ ለአገልግሎት ለማብቃት ስራዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

"ለዚህም 32 አባላትን ያካተተ 4 የጥገና ባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ በምዕራብና ሰሜን ጎንደር፣ በወሎና በሸዋ ግንባር እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል" ብለዋል።

ዶክተር ማማሩ እንዳሉት፤ አሸባሪ ቡድኑ በ28 የውሃ ተቋማት ላይ ከባድ፣ በ75 የውሃ ተቋማት ላይ ደግሞ ቀላል ጉዳት ማድረሱን በቅድመ ዳሰሳ ጥናት ተረጋግጧል።

ለውሃ ተቋማት አገልግሎት የሚሰጡ ጄኔሬተሮችና ፓምፖችንም በቡድኑ መዘረፋቸውን ተናግረዋል።

ጉዳት የደረሰባቸውን የውሃ መሰረተ ልማቶችን በፍጥነት ጠግኖ ለአገልግሎት ለማብቃት ከ520 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶችና ከፌዴራል መንግስት ለማግኘት ቢሮው እያደረገ ያለው ጥረት በጎ ምላሽ እያገኘ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም