በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን የሚያጠናክሩ የትምህርትና ሥልጠና ማዕቀፎች ሊስፋፉ ይገባል

46

ህዳር 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታውን ሊያሳልጡ የሚችሉ የትምህርትና ሥልጠና ማዕቀፎች ሊስፋፉ እንደሚገባ በአሜሪካን በዘርፉ የተሰማሩት ዶክተር በኃይሉ ቤላሞ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቱን ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ለማቀላጠፍ የሚያስችል ለአምስት ዓመት የሚቆይ ብሔራዊ የዲጂታል ስትራቴጂ የዛሬ ዓመት ገደማ አውጥቶ ወደ ሥራ ገብቷል።

ስትራቴጂውም በዋናነት የአገሪቱን ሁሉን አቀፍ የእድገት ምህዋር በቴክኖሎጂ ለመደገፍና አገሪቱ በተለያዩ ሴክተሮች የጣለቻቸውን የእድገት ግቦች በአጭር ጊዜ ለማሳካት ያለመ ነው።

በኢትዮጵያ የተጀመረው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ተስፋ ሰጪና ከጅምሩ አበረታች እንቅስቀሴዎች የታዩበት መሆኑን በአሜሪካን በዘርፉ የተሰማሩት ዶክተር በኃይሉ ቤላሞ ለኢዜአ ተናግረዋል።  

ይህ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለአገሪቱ እድገት መፋጠን ትልቅ እምርታ እንዳለው ጠቁመው ዘርፉን በእውቀት ሊመራ የሚችል የሠለጠነ የሰው ኃይል በስፋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ለዚህም የትምህርትና ሥልጠና ማዕቀፎች ሊስፋፉ እንደሚገባ ነው ዶክተር በኃይሉ የተናገሩት።

በሌላ በኩል የዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፉን በተፈለገው ደረጃና መጠን ለማስፋፋት መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ይበልጥ ተሳትፏቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም ነው ያስረዱት።

በአሁኑ ወቅት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለግሉ ዘርፍ እድገት ጭምር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፤ ባለኃብቱ ወደዚህ የቴክኖሎጂ ምዕራፍ ሊሸጋገር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ባለኃብቱ ዲጂታል ኢኮኖሚውን እንዲቀላቀል ደግሞ መንግሥት የቴክኖሎጂ አቅርቦት ከማመቻቸት በዘለለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በዘርፉ በቂ እውቀትና ክህሎት ያላቸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የአገሪቱ ዲጂታል ኢኮኖሚ እንዲጠናከር የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

መንግሥትም በዘርፉ ለተሰማሩና በቀጣይ ለሚሰማሩ የግል ሴክተር ተዋናዮች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ፣ አሰራሮችን ማሻሻልና ማቅለል እንደሚጠበቅበትም ምክረ ኃሳባቸውን ሰጥተዋል። 

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም