ከሌሎች ሀገራት ስህተት ምን እንማር?

54

በሄኖክ ታደለ

ብልህ ከሌሎች ስህተት - ሞኝ ግን ከራሱ ይማራል እንዲሉ፡፡ ሀገራችን የገጠማትን ወቅታዊ የሕልውና አደጋና የውክልና ጦርነት ተጋፍጦ ማሸነፍ የግድ ነው፡፡ አለያም  ሌሎች ሀገራት ከስህተታቸው ተምረው ፈተናውን በአሸናፊነት ከተወጡት ወይንም ስህተታቸውን ሳያርሙ ቀርተው ለባእዳን  መጫወቻ ሆነው ከቀሩ ሀገራት የምንማርበት ግዜ በመሆኑ ፡፡  የቅኝ ግዛት አራማጅ አንዳንድ የምእራብ ሀገራት የሌሎች ሀገራትን የተፈጥሮ ሀብት ለመቀራመትም ሆነ የተጽእኖ ክልላቸውን ለማስፋት የሚከፍቷቸው ጥቃቶች እየዘመኑ ይሂዱ እንጂ መሠረታዊ ይዘታቸው ተመሳሳይ በመሆኑ የጥቃቱን መንገድ እና የምእራባውያኑን አመክኒዎ መረዳት እነርሱ ሊከፍቱ የሚችሉትን ጥቃት ለመቀልበስ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡

ራሳቸውን የዴሞክራሲ ጠበቃ አድርገው በሚስሉ አንዳንድ ጽንፈኛ ምእራባውያን መንግሥታት ጣልቃ ገብነት  የሀገራትን ብሩህ ተስፋ አጨልሞአል ፡፡ ምእራባውያኑ ከምንም ነገር በላይ ስለዴሞክራሲ እና ሰብአዊ መብት የሚጨነቁ ይምሰሉ እንጂ  ከዚህ በተቃራኒ በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ በተመረጡ መሪዎችና ዴሞክራሲን ባሰፈኑ ሀገራት ላይ ጣልቃ በመግባት የግል ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ያለ እረፍት ይሰራሉ  ፡፡

ይህን የምእራባውያን  ሴራ ተረድተው የወሰዱትን መፍትሄ መመርመር እና በጉዳዩ ላይ የሕዝባችንን ንቃተ ሕሊና ይበልጥ መጨመር የውጪ ኃይላትን ጥቃት ለመመከት በእጅጉ ይረዳል፡፡ በመሆኑም በተከታታይ ጽሑፎቼ በቀጥታ ከኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ጥቃት ከተከፈተባቸው ሀገራት ልንማር የሚገቡንን ፍሬ ሃሳቦች ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር ከ1951-1953 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ኢራንን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ዶክተር ሞሃመድ ሞሳዴግ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር የሚመሳሰሉ በርካታ ጉዳዮች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ ደራሲ ፣ ታዋቂ ፖለቲከኛ ፣ዲያስፖራ፣ የሕዝብ ምክር ቤት እንደራሴ እና ሀገር ወዳድ የለውጥ ሃዋርያ መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡ በስልጣን በቆዩባቸው ሦስት አጭር ዓመታት የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት የሆነችውን ሀገራቸውን ዳግም የስልጣኔ ማማ ላይ ለማውጣት ፈጣንና ተከታታይ ለውጦችን አምጥተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የማህበራዊ ዋስትና መድህን ፣ የገቢ ግብር ጭማሬ እና የመሬት ስሪት አዋጅ ይገኙበታል፡፡ ይሁንና ጠቅላዩ በነዳጅ ሀብት የበለፀገችው ሀገራቸው የሚመጥናት ዴሞክራሲ እንድትገነባ ለያዙት ውጥን እንደ አጋዥና ብርቱ አርአያ በቆጠሯቸው ምእራባውያን ተከድተው ገና በሦስት ዓመት የስልጣን ቆይታቸው በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን እንዲነሱ ተደረገ - ምእራባውያኑ ይህ አልበቃ ብሏቸው ሞሳዴቅ ቀሪ ዘመናቸውን በወህኒ ቤትና በኋላም በመኖሪያ ቤታቸው በቁም እስር እንዲያሳልፉ አስደረጉ፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በምህጻሩ ቢፒ ማለትም ብሪቲሽ ፔትሮሊየም ተብሎ የሚጠራው እጅግ ግዙፉ ነዳጅ አምራች ኩባንያ ከ1913 ጀምሮ በኢራን ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ ያመርት ነበር፡፡ ይሁንና እጅግ በበዙ የብሪታንያ ባለሙያዎች የሚዘወረው ኩባያው ከሚያገኘው ሕልቆ መሳፍርት ገቢ ለኢራን መንግሥት የሚከፍለው የገቢ ግብርም ሆነ የሮያልቲ ክፍያ እጅግ ዝቅተኛ ነበር፡፡ ከኩባንያው ጋር የተደረገው ስምምነት ፍትሃዊ እንዳልነበር የተረዱ የኢራን ዲያስፖራ አባላትና ልሂቃንም ባገኗቸው መድረኮች ሁሉ ኩባንያው ከትርፉ ገሚሱን ለኢራን እንዲያካፍል ይጎተጉቱ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሳዴግ በፓርላማው እንደተመረጡ በገንዘብ እጦት ሳቢያ የሀገሪቱን መሠረተ ልማት ለማዘመን ያቀዱት ውጥን ተግባራዊ ማድረግ ተሳናቸው፡፡ ይህም የኢራን የተፈጥሮ ሀብት ያለቅጥ በመመዝበር ላይ መሆኑን አመላከታቸው፡፡ በመሆኑም ሞሳዴግ ኩባንያው በአስቸኳይ የሂሳብ መዝገቡን በኢራናውያን የሂሳብ አዋቂቆች እንዲያስመረምር አዘዙ፡፡ ይሁንና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማሳሰቢያ እንደትልቅ ድፍረት የቆጠረው ኩባንያው ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ፡፡ ሞሳዴግ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጡም ንብረትነቱ የብሪታንያ መንግሥት የሆነው ይኧው ኩባንያ በጄ አላለም፡፡

በመሆኑም ቆራጡ ሞሳዴግ ኩባንያው በኢራን መንግሥት እንዲወረስ እና በምትኩ የኢራን መንግሥት የነዳጅ ዘይት አምራች ኩባንያ እንዲቋቋም ወሰኑ፡፡ የሀገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የጠቅላይ ሚኒስትሩን የውሳኔ ሀሳብ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ፡፡ ዴሞክራቱ እና ሕዝባዊ ተወዳጅነት ያተረፉት ሞሳዴግ የሀገራቸውን ጥቅም ለአዲሱ ዘመን ቅኝ ገዢዎች አሳልፈው ባለመስጠታቸው ቁጥር አንድ የምእራባውያን ጠላት ተደረጉ፡፡

የምእራባውያን መገናኛ ብዙሃን ዛሬ ኢትዮጵያ ላይ እንዳደረጉት ሌት ተቀን ስማቸውንና ሀገራቸውን በማጠልሸት ሥራ ላይ ተጠመዱ፡፡ የቴህራን ውሳኔ የዓለም ሰላምን የሚያውክ ይመስል የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትም በምእራባውያን ጫና በኢራን ውሳኔ ላይ ተደጋጋሚ ውይይት አደረገ ፡፡ ዶክተር ሞሳዴግ በፀጥታው ምክር ቤት መድረክ በመገኘት የኢራን ውሳኔ ከፀጥታው ምክር ቤትም ሆነ ከአካባቢያዊ ሰላም ጋር ምንም እንደማያገናኘው ሞገቱ፡፡ ይሁንና ዘግይቶ በብሪታንያ እና አሜሪካ ጫና የኢራን ነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ በዓለም ገበያ ላይ እንዳይሽጥ ማእቀብ ተጣለ፡፡

የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዊኒስተን ቸርችል ኢራን ለማእቀቡ ባለመንበርከኳ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለነበሩት ድዋይት አይዘንሃወር ሞሳዴግን በአስቸኳይ ከስልጣን ለማንሳት ፈጣን ትብብር እንዲያደርጉላቸው የተማጽኖ ደብዳቤ አስገቡ፡፡ ሞሳዴቅ መጥፎ ምሳሌ በመሆናቸው እርሳቸው ዝም ከተባሉ በመካከለኛው ምስራቅም ሆነ በደቡብ አሜሪካ የሚገኙ የሀገራት በአሜሪካና ብሪታንያ ኩባንያዎች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ይህ ደግሞ የምእራባውያንን ጥቅም እንደሚጎዳ ሞገቱ፡፡ አይዘንሃወር ለቸርችል ደብዳቤ ወዲያውኑ ነበር አውንታዊ ምላሽ የሰጡት፡፡

የሁለቱ ሀገራት የስለላ ድርጅቶች በመተባበር ፣ዘጠኝ አውቶቡስ ሙሉ የውሎ አበል ተከፋይ የሆኑ አርቴፊሺያል ተቃዋሚዎችን ወደ ቴህራን ከተማ በሕቡእ ተልእኮ በማስገባትና በሞሳዴቅ ላይ ሕዝባዊ ተቃውሞ የተነሳባቸው በማስመሰል ስኬታማ መፈንቅለ መንግሥት አስደረጉ፡፡ በምትካቸውም አፍቃሪ ምእራባዊው ጄኔራል ፋዚላህ ዛህዲ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ያዙ፡፡ ሀገር ወዳዱ፣ የለውጥ ኃዋርያውና  ዲሞክራሲ አቀንቃኙ ዶክተር ሞሳዴቅ ባልጠበቁት መንገድ ወደ ወህኒ ተወርውረው ቀሪ ዘመናቸውን በቁም እስር አሳለፉ፡፡

በአንጻሩ በምእራባውያን የተደገፉት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሂዲ ሀገሪቱን ለዘመናት ሲመዘብር የቆየው አንገሎ ፐርሺያ ኦይል ካምፓኒ ዳግም በኢራን ሥራ እንዲቀጥል ፈቀዱ፣ ኢራንም የኩባንያውን የሂሳብ መዝገብ ዳግም ላትመረምር ውል ተፈራረመች፡፡

ጉዳዩን በጥልቀት መመርመር የሚፈልግ ሰው ካለ የአሜሪካው ማእከላዊ የስለላ ድርጅት (ሲ አይ ኤ ) ከ64 ዓመታት በኋላ ኦፕሬሽን አጃክስ ተብሎ ስለሚጠራውና ሞሳዴግን ከስልጣን ስላስወገደው ሚስጥራዊ ተልእኮ ከአንድ ሺህ ገጽ በላይ ሚስጥራዊ ሰነዶች ይፋ ያደረገ በመሆኑ ማንበብ ይችላል፡፡ ብዙሃኑ የኢራን ሕዝብ ተወዳጁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሳዴግ በውጪ ኃይሎች ሴራ እና በተገዙ ቅጥረኛ የእለት አበል ተከፋይ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ከስልጣን መነሳታቸውን ፈጥኖ አልተረዳም ነበር፡፡

ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ  ለእለት አበል እንጂ እውነተኛ የለውጥ ሀሳብ ያልነበራቸው በመሆኑ የምዕራባውን ፍላጎት አሳክተው ወደ ቤታቸው ተመለሱ ፡፡ በወቅቱም የሕዝቡ ንቃተ ሕሊና የጥቃቱን  ሴራ ለመረዳት  ባለመቻሉ  ተወዳጁን ጠቅላይ ሚኒስትር ከምእራባውያን ጥቃት መታደግ አልተቻለም፡፡ እርሳቸው ሲታሰሩ ለኢራን ልማትና ዴሞክራሲ ያሰቧቸው ውጥኖች በሙሉ በእንጭጩ ተቀጩ፡፡ በእርሳቸው ከስልጣን መነሳት የሀገሪቱ ተስፋ በጠራራ ፀሐይ ተነጠቀ፡፡

የኋላ የኋላ ኢራናውያን  ከረፈደ  ሴራውን ቢረዱም  ሞሳዴግን ከሲአይኤ ተንኮል ባለማስጣላቸው ቁጭት ውስጥ ወደቁ፡፡ የምእራባውያኑ ጣልቃ ገብነት ውጤቱ ምን ይሆን ካላችሁ ደግሞ በቀጠሉት 26 ዓመታት ኢራናውያን በከፋ ድህነት ሲኖሩ በአንጻሩ የሀገሪቱ የተፈጥሮ ጋዝና የነዳጅ ዘይት ሀብት ያለከልካይ ተመዘበረ፡፡ ከምዝበራ በተረፈው ጥቂት ገንዘብም በአሜሪካ እገዛ ወደ ንግሥናቸው የተመለሱት የሀገሩ ንጉሥ ኢራናውያንን ዘንግተው በየከተሞቹ ቅንጡ ቤተመንግሥታትን ያስገነቡ ጀመር፡፡ የንጉሡ ቅጥ ያጣ የኑሮ ዘዬ በምእራባውያን መገናኛ ብዙሃን ከመወገዝ ይልቅ እየተቆለጳጰሰ ነበር የሚቀርበው፡፡ ይሁንና በነዚያ 26 የጨለማ ዘመናት ከኢራን ተራማጅ ልሂቃን እስከ ኃይማኖት መሪዎች ድረስ ሀገራቸው በምእራባውያን ሴራ የገባችበትን ቅርቃር ሕዝባቸው እንዲረዳ መሥራታቸውን ቀጠሉ፡፡

የኢራን ሕዝብ መንቃት ሲጀምር የዘመናት ቁጭት እና የሀገሩ ምዝበራ ያንገበግበው ጀመር፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ ሊታመን የማይችል የምእራባውያን ጥላቻን አረገዘ፡፡ ሞሳዴግን ማዳን ባለመቻሉም ትልቅ ቁጭት ውስጥ ገባ፡፡

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1979 በታላቅ ቁጣ ወደ ጎዳና በመውጣት አብዮት አፈነዳ፡፡ ሀገሪቱም ከዘመናት ምዝበራ በኋላ የተፈጥሮ ሀብቷን ዳግም ተቆጣጠረች፡፡ ዴሞክራሲ ለምእራባውያን ዝርፊያ ሊያጋልጠን ይችላል ብለው የፈሩት ኢራናውያን እስላማዊ መንግሥት መሠረቱ፡፡ ይህ የኢራናውያን ተግባር ስህተት ከሆነ ከበርካታ የአውሮፓ ሀገራት አስቀድሞ የነበራቸው ዓለማዊ ዲሞክራሲ የመመሥረት ውጥን እና የዴሞክራሲ ተስፋ በምእራባውያን በመክሸፉ ነው ሃይማኖታዊ መንግሥት ለመመሥረት የተገደዱት፡፡ ያም ሆነ ይህ ኢራናውያን እንደ አውሮፓ የዘመን አቆጣጠር ከ1979 ጀምሮ መጻኢ እድላቸውን በእጃቸው ካስገቡ ወዲህ ያንን ሁሉ የኢኮኖሚ ማእቀብ ተቋቁመው እጅግ ግዙፍ ኢኮኖሚ ከመገንባት አልፎ በበርካታ የሳይንስ ዘርፎች ቀዳሚ ለመሆን በቅተዋል- ከነዚያም መካከል የድሮን፣ሚሳኤል እና የኒውክሌር ቴክኖሎጂዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ኢራን ከከርሰ ምድሯ ነዳጅ እንዳታወጣ ለማድረግ ምእራባውያን ለሀገሪቱ ምንም አይነት ነዳጅ ለማውጣት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች እንዳይሸጡ ቢያግዱም ኢራናውያን በዚያ ተስፋ አልቆረጡም፡፡ ከምእራባውያን የሚተካከል ሀገር በቀል ቴክኖሎጂን በሀገር ቤት በማምረት እስከ ዛሬ ድረስ ዋነኛ ከሚባሉ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ አምራች ሀገራት መካከል ይገኙበታል፡፡

ፍትሃዊ በሆነ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጣውን የኢትዮጵያን መንግሥት አስወግዶ ባልተመረጠ ተላላኪ መንግሥት ለመተካት በቅርቡ የተደረገው የዙም ውይይት ይፋ በመውጣቱ ተደስቻለሁ፡፡ ምስጋና ለእውነተኛው ጋዜጠኛ ጄፍ ፒርስ ይሁንና ቪዲዮው ሀገራቸውን ለሚወዱ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ስጦታ ነው፡፡ በመሆኑም የገዢው ፓርቲ ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚ በሕዝባዊ ምርጫ ስልጣን የያዘውን መንግሥት ልንጠብቅ ይገባል፡፡ ይህንን ማድረግ የፓርቲ መስመር ውሳኔ ሳይሆን በሀገር ላይ የተቃጣን ወረራ መቀልበስ ነው - የሀገርና ዜግነት ክብር የማስጠበቅ ጉዳይ በመሆኑ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም