ቀጥታ፡

የወገን ጦር የህወሃት አሸባሪ ቡድን ይዟቸው የነበሩት ጋሸና እና ጭፍራ መቆጣጠሩ ለቀጣይ ግዳጅ ትልቅ ፋይዳ አለው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 22/2014 (ኢዜአ) የወገን ጦር የህወሃት አሸባሪ ቡድን በወረራ ይዟቸው የነበሩ ጋሸና እና ጭፍራን መቆጣጠሩ ለሰራዊቱ ቀጣይ ግዳጅ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው የቀድሞው ጦር ሰራዊት ከፍተኛ መኮንን ብርጋዴር ጀኔራል ካሳ ወልደሰማዕት ተናገሩ።

የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ በግንባር በመገኘት ሰራዊቱን መምራት ከጀመሩ በኋላ እየተመዘገበ ያለውን ወታደራዊ ድልም አድንቀዋል።

የቀድሞ ጦር ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኑ ብርጋዴር ጀኔራል ካሳ ወልደሰማዕት፤ በኮንጎ ሰላም ማስከበር ዘመቻ ከጠቅል ብርጌድ ዘማቾች መካከል ነበሩ።

በታሪካዊቷ ኢሉባቦር ጎሬ የተወለዱት የጦር መኮንኑ፤ በአሜሪካው ፎርቲ ሲ ኦክሎሀማ በመድፈኛና የተማሪ ሚሳኤል ትምህርት ቤትን ጨምሮ በአሜሪካና በሩሲያ ወታደራዊና ሌሎች ትምህርቶችን ቀስመዋል።

በኮንጎ የተመድ ሠላም አስከባሪ ጦር ውስጥ በኢትዮጵያ ወገን የዘመተው የክቡር ዘበኛ የጠቅል ብርጌድ አባልም ነበሩ።

በቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት በተለያዩ ኃላፊነቶች ለ34 ዓመታት አገራቸውን በብቃት አገልግለዋል።

የካበተ ወታደራዊ ልምድ ባለቤት የሆኑትን የጦር መኮንን የአገር መከላከያ ሰሞኑን እያስመዘገበ ያለውን ውጤታማ የድል ግስጋሴ በማስመልከት ኢዜአ አነጋግሯቸዋል።

የወገን ጦር በሁሉም ግንባሮች እያስመዘገበ ያለውን ድል በማድነቅ የጀመሩት ብርጋዴር ጀኔራል ካሳ ወልደሰማዕት፤ የህወሃት አሸባሪ ሃይል በወረራ ይዟቸው የነበሩትን ጋሸና እና ጭፍራ ሰራዊቱ መቆጣጠሩ ለቀጣይ ግዳጆች ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።

ለድሉ ስኬት ከሰራዊቱ ቁርጠኝነት በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በግንባር ተገኝተው መምራታቸው ለላቀ ውጤት ማብቃቱን ጠቅሰዋል።

ወደ ጦር ግንባር ካመሩ በኋላ የመጣው ተከታታይ ድል ጦር መሪው ከጎኑ ሲሆን ሞራሉ እንደሚያድግ ያረጋገጠ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች የጋራ ድል አድራጊነት በጠላት ሃይል ላይ ሽንፈትና ኪሳራ ከማድረሱ በተጨማሪ ጠላት ሞራሉ እየወደቀ በመበታተን ላይ መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል።

በአንጻሩ የወገን ጦር በላቀ ወኔ እና ሞራል ታጅቦ በሎጂስቲክስና በአደረጃጀት ተጠናክሮ በአስተማማኝ ደጀን ህዝብ እየታገዘ በመሆኑ ከድል ግስጋሴ የሚያቆመው አይኖርም ይላሉ።

በቀጣይም ሰራዊቱ ስትራቴጂክ ቦታዎችን የመቆጣጠር ሂደቱን አጠናክሮ በመቀጠል ኢትዮጵያን በአሸባሪው ህወሃት ከተደቀነባት የህልውና ስጋት ነፃ ማድረግ አለበት ብለዋል።

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫው፤ በጋሸና ግንባር ጋሸና፣ አርቢት፣ አቀትና ዳቦ ከተሞች፤ በወረኢሉ ግንባር ደግሞ የጃማ ደጎሎ፣ ወረኢሉ፣ ገነቴ፣  ፊንጨፍቱ፣ አቀስታ ከተሞች በጀግኖች የመከላከያ  ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ተጋድሎ ነጻ ወጥተዋል።

በተመሳይ በሸዋ ግንባር ደግሞ መዘዞ፣ ሞላሌ፣ ሸዋሮቢትና ራሳ አካባቢዎች ከወራሪው ቡድን ነጻ እንደወጡም እንዲሁ ።

በምስራቅ ግንባር በጀግናው መከላከያ ሰራዊት፣ አፋር ልዩ ሃይልና ሚሊሻ የተቆጣጠራቸው ጭፍራ፣ ካሳጊታ፣ ቡርቃና ሌሎች አካባቢዎችን ከጠላት በማጽዳት የመንግስት መዋቅርን መልሶ የማደራጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በሁሉም ግንባሮች እየተመታ የሚሸሸው አሸባሪ ሃይል በተስፋ መቁረጥ ዘረፋና ውድመት እንዳይፈጽም በየአካባቢው ያለው ኀብረተሰብ ተደራጅቶ ራሱንና አካባቢውን እንዲጠብቅ፣ ጠላትን እንዲማርክ እና እጅ በማይሰጡት ላይ ደግሞ እርምጃ እንዲወስድ  መንግስት ጥሪ አቅርቧል።

በግንባር ጦር እየመሩ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ሠራዊቱ በከፍተኛ ሞራል ላይ እንደሚገኝ እና በአጠረ ጊዜ፤ በአነስተኛ መሥዋዕትነት የኢትዮጵያ ድል እንደሚረጋገጥ መግለጻቸው ይታወሳል።

"የኢትዮጵያ ፍላጎት ሰላምና ልማት ነው፤ ወደዚህ ጦርነት የገባነው ተገደን ነው፤ ማሸነፋችን ግን አይቀሬ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለአሸባሪው ህውሓት የተሰለፉ ሁሉ እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም