በመከተብና አስፈላጊውን የጥንቃቄ መንገድ በመተግበር ባህሪውን የሚቀያይረውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በመከተብና አስፈላጊውን የጥንቃቄ መንገድ በመተግበር ባህሪውን የሚቀያይረውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል ይገባል

አዲስ አበባ፣ህዳር 22/2014 (ኢዜአ) ኀብረተሰቡ ክትባት በመውሰድና አስፈላጊውን የጥንቃቄ መንገድ በመተግበር በየጊዜው ባህሪውን እየቀያየረ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል እንዳለበት የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ አስጊነቱ እየጨመረ የመጣውን የኮቪድ ወረርሽኝ ለመከላከል በመንግስት በኩል አስፈላጊው ቁጥጥር እየተደረገ ነው።
በተለይም አፍሪካ በአራተኛው የኮቪድ ማዕበል መጠቃት መጀመሯ እና አዲሱ የኦሚክሮን ኮቪድ ዝርያ መታየት በዓለም ደረጃ ወረርሽኙ አስጊ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል።
በመሆኑም ኀብረተሰቡ ክትባት በመውሰድና አስፈላጊውን የጥንቃቄ መንገድ በመተግበር በየጊዜው ባህሪውን እየቀያየረ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል እንዳለበት ነው ያሳሰቡት፡፡
ኀብረተሰቡ ክትባቱን በሚመለከት የሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎችን መቀበል እንደሌለበትም ተናግረዋል፡፡
ክትባቱ በዓለም ደረጃ ደህንነቱ የተረጋገጠና ቀደም ብለው የተከሰቱትን የኮቪድ ዝርያዎች በመከላከል ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ህብረተሰቡ ይህንን ግንዛቤ በመውሰድ ለክትባት ዘመቻው እንዲተባበርና እንዲከተብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተለይም አራተኛው የኮቪድ ወረርሽኝ ማዕበልና አዲሱ የኮቪድ ዝርያ ለመከላከል ወደ ሃገሪቱ የሚያስገቡ በሮች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም አምስት ቀን የሞላው የምርመራ ሰርተፍኬት ተቀባይነት ያገኝ እንደነበር አስታውሰው፤ ወረርሽኙን ለመከላከል ሲባል ቀነ ገደቡን ለማሳጠር እየተሰራ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
በተጨማሪ ፣ያልተከተቡ ሰዎች እንዲከተቡ የማድረግና ሌሎች ቁጥጥሮችን ለማጥበቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የኮቪድ መከላከልና ቁጥጥር መመሪያዎች እንዲከበሩ የማድረግና የክትባት ዘመቻውን ማስፋፋት ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
እስካሁን በተደረገው የክትባት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መከተባቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።