ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

89

መተማ ህዳር 22/2014 (ኢዜአ) በሱዳን ገዳሪፍ ግዛት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአሸባሪው ህወሓት የጭካኔ ድርጊት ከቄያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።
በገዳሪፍ ግዛት የአማራ ልማት ማህበር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አማካኝነት ከኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተሰበሰበውን ድጋፍ የምዕራብ ጎንደር ዞን የህልውና ዘመቻ የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ተረክቧል።

የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ተወካይ አቶ ካሊድ ሳልህ በርክክቡ ላይ እንዳሉት በድጋፍ ማሰባሰብ ስራው 150 ሺህ ብር ግምት ያለው አልባሳትና የምግብ ማብሰያ ቁሶችን ለተፈናቀሉ ወገኖች ማበርከት ተችሏል።

በተጨማሪም በጥሬ ገንዘብ 61 ሺህ ብር መለገሱን ተናግረዋል ።

''ህዝባችን የገጠመው ችግር የእኛም ጉዳት ነው'' በሚል መሪ ሀሳብ ድጋፉ መሰብሰቡን የገለጹት ተወካዩ  በቀጣይም ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ የማተስተባበር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን የህልውና ዘመቻ ሀብት አፈላላጊ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ደረሰ አዱኛ በወቅቱ እንዳሉት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን  በያሉበት ሆነው ተጎጂዎችን ለመደገፍ የሚያደርጉት ጥረት የሚደነቅ ።

በሱዳን ገዳሪፍ ግዛት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ሀብት አሰባስበው ድጋፍ ማድረጋቸው ተፈናቃይ ወገኖችን ወደ ነበሩበት ህይወት ለመመለስ የሚሰራውን ስራ እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።

ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም