ቀጥታ፡

የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ሸሽተው እንዳያመልጡ ሕዝቡ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ባህርዳር ህዳር22/2014 (ኢዜአ) የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች የዘረፉትን ሀብት ንብረት ይዘው እንዳይሸሹ ሕዝቡ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥሪ አቀረቡ።

ርዕሰ መስተዳድር  ዶክተር ይልቃል ከፍአለ  በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

አሸባሪው ህወሓት በአማራ አዋሳኝ አካባቢዎችን በእብሪት ወሮ በንጹሃን ዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን መፈጸሙን፣ ሀብት ንብረት ማውደሙን ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው አመልክተዋል።

አሸባሪው ህወሓት በሀገር ላይ የደቀነውን ወቅታዊ የሕልውና አደጋ በአጠረ ጊዜ ለመቀልበስ እየተደረገ ባለው ትግል የክልሉ ሕዝብና የፀጥታ አካላት ከጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን የሚጠበቅባቸውን መወጣታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር ሕዝቡ በግንባር ይህን የሽብር ቡድን በጀግንነት እየተፋለሙ ላሉ ውድ የኢትዮጵያ ጀግኖች ከስንቅ ዝግጅትና አቅርቦት ጀምሮ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል።

የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች በእብሪት በክልሉ አዋሳኝ በሆኑ አካባቢዎች  የዘረፉትን ሀብት ንብረት ይዘው እንዳይሸሹ ጠቅላይ ሚነስትር ዐብይ አህመድ ባስገነዘቡት መሰረት ሕዝቡ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲፈጽም አሳስበዋል።

የሽብር ቡድኑን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች በንቃትና ጥንቃቄ በመከታተል ከተቻለ በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ አድርጎ በቁጥጥር ስር እንዲያውላቸው ካልሆነም እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል።  

ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል በመግለጫቸው የሀገር ሉዓላዊነትና የህዝቡ ደህንነት በዘላቂነት የሚረጋገጠው ጠንካራ የመከላከያ ኃይል በማደራጀትና በመገንባት መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም የክልሉ ውጣቶች ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ተቀላቅለው የሀገር አለኝታነቸውን እንዲያረጋግጡም ጠይቀዋል።

ለዚህም "አካላዊ ብቃታችሁ፣ የትምህርት ዝግጅታችሁና ነባራዊ ሁኔታችሁ የሚፈቅድላችሁ የክልሉ ወጣቶች የሀገር አለኝታ የሆነውን የመከላከያ ተቋም መቀላቀል አለባችሁ" ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሀገራችን ላይ ሊቃጣ የሚችለውን ማንኛውን አፍራሽ ተልዕኮ በመመከት የሀገር ሕልውና እና ሉዓላዊነት ዋነኛ ዘብ መሆኑን ወጣቶች ተገንዘብው ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም