የፓን አፍሪካኒዝም ብርታት-ኢትዮጵያ

77

የሰውነት ቆዳ ቀለም መለያየት ከአንድ አብራክ የተፈጠሩ ሰዎችን የበላይና የበታች አድርጎ እንዲያስቡ ነጮችን አደረገ። ባለነጭ ቆዳ ቀለሞቹ፤ ነጮቹን ማለቴ ነው፤ ጥቁር የተባለ ሁሉ እንደ እነሱ ሰብዓዊ ፍጡር ሳይሆን ባሪያቸውና ተላላኪያቸው እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል።

በተፈጥሮ ጥቁር የሆኑት አፍሪካዊያን አሉታዊ አስተሳሰባቸው መተግበሪያ እንዲሆኑ ብዙ ሰርተዋል።

ጥቁሮች የራሴ መብት፣ የግሌ ሀብት፣ የእኔ ሀሳብ የሚሉት ነገር እንዲኖራቸው አይፈልጉም። እኔ ካልኩት ውጭ በሚል የበታች አድርገው መርገጥ ያምራቸዋል። አድርገውታልም።

ይህ አብዝቶ ያስጨነቃቸው ጥቁሮች በሀገረ አሜሪካ የነፃነት ጩኸት ማሰማት ጀመሩ፤ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ። ንቅናቄው በዋናነት የቅኝ ግዛት መስፋፋትን ወይም የነጮች የበላይነትን በመዋጋት የአፍሪካን አንድነት ለማጠናከር የታሰበ ነው።

ፓን አፍሪካኒዝም በአሜሪካ ምድር ይጠንሰስ እንጂ፤ የንቅናቄው መንፈስና ብርታት ኢትዮጵያ እንደነበረች ታሪክ ያወሳል።ለዚህም ነው ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ኩራት የጀግንነት ተምሳሌት ተደርጋ የምትገለጸው። የፓን አፍሪካኒዝም ግቡ ጠንካራ አፍሪካዊት ሀገር መመስረት ነበርና ለነጮች ያልተንበረከከችና ቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ ነፃነቷን ጠብቃ ያለች ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗን አምነው ተንቀሳቅሰዋል።

የአፍሪካ ሀገሮች የማዕዘን ድንጋይ ሆና መታየቷ ከጎኗ እንዲቆሙ  አድርጓቸዋል። በዚህም የኢትዮጵያ ነፃነት የአፍሪካ ብሎም የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ተደርጎ ይወሰዳል። በተመሳሳይ ጉዳቷን ጥቃቷም የእነርሱ ህመም ነው። አሁን ያለው ኢትዮጵያን ደካማና የተበተነች ሀገር በማድረግ የአፍሪካን ነፃነት ለመንጠቅ እየተደረገ ያለውን የእጅ አዙር ጦርነት በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ መዋጋት እንደሚያስፈልግ ምሁራን ይናገራሉ።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሰቲ የታሪክ መምህር ዓለማየሁ አብርሃም እንደሚሉት ኢትዮጵያ ጥቁር ሆና በታሪክ ነጮችን በማሸነፍ የጥቁሮችን ነፃነትና የእችላለሁ መንፈስ በደማቅ ቀለም ጽፋለች። ይህ ደማቅ ታሪኳ ለመላው ጥቁሮች የአንድነት እንቅስቃሴ (ፓን አፍሪካኒዝም) ስንቅ ነው ይላሉ። "ይህን በማጥፋት ሌላ ታሪክ ለመጻፍ በአሸባሪው ህወሓት በኩል ጦር የመዘዙ ምዕራባውያንን መዋጋት ከመላው ጥቁር ህዝቦች ይጠበቃል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያላት ጀግንነት በታሪክ የሚቀር በትውልድ የሚቋረጥ አይደለም ያሉት መምህር አለማየሁ፣ በአድዋ ጦር ግንባር ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዙፋናቸውን ትተው በመዝመት ተዋግተው ጣሊያንን አሳፍረዋል። ያን ታሪክ ማሰብ ያልቻሉ ምዕራባውያን ደግሞ ዛሬ በአሸባሪውና ወራሪው ህወሓት ካባ ተሸሽገው ኢትዮጵያን ሲወጉ በቤተመንግሥት መቀመጥን ያልሻተ መሪዋ በጦር ግንባር ተከስቷል። ታሪክ ራሱን እነደሚባለው ራሱን ደግሞ አሳይቶናል። የሕልውና ጦርነቱም በኢትዮጵያ አሸናፊነት በአጠረ ጊዜ ድል እንደሚጠናቀቅ መላው ኢትዮጵያውያን ፍጹም እርግጠኞች ናቸው።

በተለያየ ዘመነ መንግሥታት የመጡ የውጭ ወራሪ ሀይሎችን በአንድ ጥሪ ወጥቶ ዶግ አመድ በማድረግ የሚታወቁ ህዝቦቿም ከዳር እስከ ዳር በወኔ ተነስተው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተው የህልውና ትግሉን ተቀላቅለዋል፤ እየተቀላቀሉም ነው። የአፍሪካ ሀገሮችም ይህ ጦርነት የኢትዮጵያ ብቻ አለመሆኑን ተረድተው ከኢትዮጵያ ጎን ቆመው መዋጋትና የፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ እንዲላበሱ አሳስበዋል። ''ይህን ጦርነት ማሸነፍ የአፍሪካ ነጻነት መጠበቅ ነው'' እንዲሉ።

እነርሱ እንደፈለጉ የሚያዙትና የሚጋልቡት መንግሥት በአፍሪካ እንዲፈጠር ይፈልጋሉ፤ ኢትዮጵያ ደግሞ አይሆንም የእኛ ጉዳይ እኛ እናውቃለን በማለት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን መወከሏ ምቾት አልሰጣቸውም ይላሉ ምሁሩ። ቀድሞ ኢትዮጵያን በመበተን አፍሪካን እንደፈለጉ የማድረግ ዓላማ ይዘዋል። የፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ  ማራመድ ያስፈልጋል ይላሉ መምህር ዓለማየሁ። "የአፍሪካ መቀመጫን ማፍረስ አፍሪካን ማፍረስ ነው፤ የአፍሪካ ኅብረትም የተለየ እንቅስቃሴ ማድረግና ድርጊቱን የሚቃወም መግለጫና መልዕክት ለጥቁር ህዝቦች ማስተላለፍ አለበት" ሲሉም ያክላሉ።

በዩኒቨርስቲው የሥነ ዜጋ ትምህርት ክፍል መምህር ሙሉቀን አየለ እንደሚሉት፤ ሌሎችን ለነፃነት የምታስተባብር አፍሪካዊት ሀገር በክብር እንድትኖር በነጮች አይፈለግም። ኢትዮጵያን ለማፍረስ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ ፕሮጀክትን እንቅስቃሴ  ለማዳከም በግብፅ በኩል ሞክረው ስላልቻሉ ያኮረፉ ቡድኖችን በመፈለግ ጦር ሰብቀው አቀብለው አቀብለዋል ባይሳካላቸውም ቅሉ። ፍላጎታቸው አፍሪካውያን ጠንክረው ራሳቸውን እንዳይችሉ ማድረግ ነው። ዋነኛ ዓላማቸው ለአፍሪካና ለጥቁር ሕዝቦች አርዓያዋን ኢትዮጵያን በማፍረስ አፍሪካን መግዛት ነው።

በመሆኑም ፓን አፍሪካኒዝም በተጠናከረ እንቅስቃሴ መጀመር አለበት። ኢትዮጵያ ያለችበት ቀጠናና የመሪነት ሚናዋ ጦርነቱን የአፍሪካ ያደርገዋል። አዎ! እንደ ግለሰብ ሳይሆን እንደ ሀገር አፍሪካን እየተከፋፈሉ ግዛታቸውን ሲያስፋፉ አፍ እያላቸው የማይናገሩ፣ አቅም እያላቸው ምንም የማይቻሉ አድርገው ይገዙ ነበር። ዛሬ ደግሞ በቀጥታ መግዛትና መዝረፍ አልቻሉም። ያመረቱትን ሸቀጥና የፖለቲካ ፍልስፍናና እሳቤዎቻቸውን ሊያራግፉብን ይሻሉ።እኛ እናውቅላችኋለን፤ የሚበጃችሁ የእኛን ሀሳብ መቀበል ለእኛ ታዛዥ መሆን ነው ሊሉን ይዳዳሉ። ግን ይሄ ዘመን ያለፈበት ጉዳይ መሆኑን ሊረዱት አልቻሉም ወይም አልፈለጉም።

 የኢትዮጵያ ህዝብ አድዋን በአጎዋ አይለውጥም። ማንነቱንም አሳልፎ አይሰጥም። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነውና! አዎ ጮኽ ብለን እንናገራለን አፍሪካ በእጅ አዙር ቅኝ አስተዳደር አትገዛም። የራሷ ፍልስፍና፣ የራሷ ማንነት ያላት አህጉር ናትና! ለዚህ ደግሞ በቀደምት አፍሪካውያን የተጠነሰሰው ፓን አፍሪካኒዝም ማሳያ ነው። ጊዜው የአፍሪካ ትንሳኤ የሚታወጅበት ነው። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ዋጋ በመክፈል ላይ ናት። በድልም ትወጣለች። ቸር እንሰንብት!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም