በሰሜን ሸዋ ዞን ለብልሽት ተዳርጎ የነበረ መንገድ ተጠግኖ ለአገልግሎት በቃ

ደብረ ብርሃን ግንቦት 9/2010 በሰሜን ሸዋ ዞን በአገልግሎት ብዛት ለብልሽት ተዳርጎ የነበረ 408 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ተጠግኖ ለአገልግሎት መብቃቱን የደብረ ብርሃን ገጠር መንገድ ጥገና ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ታየ ሙለታ ለኢዜአ እንደገለጹት መንገዱ ተጠግኖ ለአገልግሎት እንዲበቃ የተደረገው በመደበኛና በወቅታዊ ጥገና ፕሮግራም ነው። በዚህ በጀት ዓመት 560 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመጠገን ታቅዶ በተደረገው እንቅስቃሴም የዓመቱን እቅድ 73 በመቶ ያህል ማከናወን እንደተቻለ ገልፀዋል። የተጠገነው መንገድ በአገልገሎት ብዛት፣ በክረምት ጎርፍና ናዳ ለብልሽት ተዳርጎ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ጥገና ከተደረገለት መንገድ ውስጥ ጫጫ - ጽጌሬዳ 49 ኪሎ ሜትር፣ ጭሬ - ማጀቴ 10 ኪሎ ሜትር፣ መኮይ- ጦርማሳያ 26 ኪሎ ሜትር፣ ወጀት- አስጥድ 21 ኪሎ ሜትር፣ ዓለም ከተማ - የሳ 17 ኪሎ ሜትርና ሌሎች እንደሚገኙበት አስታውቀዋል፡፡ የመንገዱ በመጠገን ለትራንስፖርት እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንና ለመንገዱ ጥገናም ከፌደራል መንገድ ፈንድ  የተገኘ 20 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ተናግረዋል። በዚሁ ጥገናም ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ የአካባቢው ወጣቶች ጊዜያዊ የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። የህዝብ ማመላለሻ መኪና ሾፌር አቶ ደግፌ በላይ  በሰጡት አስተያየት ቀደም ባሉት ዓመታት የመገድ ጥገና የሚካሄው በክረምት ወቅት በመሆኑ በተገቢው የጥራት ደረጃ ስለማይሰራ በአጭር ጊዜ ለብልሽት ይዳረግ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ዓመት በበጋው ወራት እየተካሄደ ያለው የመንገድ ጥገና ክረምት ከመግባቱ በፊት በመጠገኑ በተሽከርካሪዎችና በህብረተሰቡ ላይ የሚደርሰውን እንግልት ለመቀነስ ማስቻሉን አስታውቀዋል፡፡ በአጎለላና ጠራ ወረዳ የጽገሬዳ ቀበሌ አርሶ አደር ጌታመሳይ በላቸው በበኩላቸው በአካባቢያቸው ተበላሽቶ የነበረው መንገድ መጠገኑን ተከትሎ ለትራንስፖርት አገልግሎት ቋሚ ተሽከርካሪ በመመደቡ እንግልታቸውን እንዳስቀረላቸው ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም