አፍሪካዊያን ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የውጭ ጫና በተባበረ ክንድ ሊታገሉት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካዊያን ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የውጭ ጫና በተባበረ ክንድ ሊታገሉት ይገባል
ህዳር 21/2014 /ኢዜአ/ "አፍሪካዊያን የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ቀንዲል በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የውጭ ጫና በተባበረ ክንድ ሊታገሉት ይገባል" ሲሉ የአዲስ አበባ ባለሃብቶች ፎረም ፕሬዝዳንት አቶ አሸናፊ ሙሴ ገለጹ።
አቶ አሸናፊ ሙሴ ለኢዜአ እንደተናገሩት አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት ኢትዮጵያን በማፍረስ አፍሪካን ለማዳከም እየሰሩ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻነት ቀንዲልና ራስ መሆኗን አንስተው፤ ከዚህ አኳያ የምዕራባውያን ዋነኛ አጀንዳ የአፍሪካ ራስ የሆነችውን ኢትዮጵያን ማዳከም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
"ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እንገባለን'' ብሎ የፎከረውን አሸባሪው የህወሃት ቡድንን በማገዝ ዓላማቸውን ለማሳካት እየታተሩ መሆኑንም ነው የተናገረው።
በመሆኑም አፍሪካውያን ጉዳዩ የኢትዮጵያ ብቻ አለመሆኑን በመገንዘብ በጋራ መቆም አለባቸው ብለዋል።
ቀደምት ኢትዮጵያዊያን አባቶች የደምና የአጥንት መሰዋዕትነት ከፍለው ነጻ አገር ማቆየታቸውን ገልጸው፤ የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ወኔ ክፉዋን ለሚሹ ጠላቶች እንደማይመች ተናግረዋል።
ምዕራባውያን በተለይ ምስራቅ አፍሪካን የማፍረስ ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸውም ነው የገለጹት፡፡
ምዕራባዊያኑ አፍሪካን ለዘመናት ሲበዘብዙና ሲያዳክሙ መኖራቸውን አስታውሰው፤ አፍሪካውያን ዘመናትን የተሻገረ የጭቆና ቀንበር ተሸካሚዎች እንደነበሩ አብራርተዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ለአፍሪካ የሚቆረቆር መሪ ለእነርሱ አይመቻቸውም፤ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ጫናም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም አፍሪካውያን በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ጫና በተባበረ ክንድ ሊታገሉት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው ጦርነት ሁሉን አቀፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ በኢኮኖሚው መስክ የተሰማሩ አካላት ይህን በመገንዘብ ከዚህ ቀደም ከነበረው አሰራር በተለየ መልኩ ጠንክረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡