ለአሸባሪው ሕወሐት የተሰለፉ ሁሉ እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሳሰቡ - ኢዜአ አማርኛ
ለአሸባሪው ሕወሐት የተሰለፉ ሁሉ እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሳሰቡ
ህዳር 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለአሸባሪው ሕወሐት የተሰለፉ ሁሉ እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አሳሰቡ።
በግንባር ተገኝተው በአንደኛው የጦር ግንባር የመጨረሻ ዕቅድ ላይ የመከሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በአጠረ ጊዜና በአነስተኛ መሥዋዕትነት የኢትዮጵያ ድል የሚረጋገጥበትን መመሪያ ሰጥተዋል።
ሠራዊቱ በከፍተኛ ሞራል ላይ እንደሚገኝና ጠላትም እየተሸነፈ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹ ሲሆን፣ በተደናበረ ዕቅድ የገባው ጠላት ተደናብሮ መውጣት እንደማይችል ተናግረዋል።
ለአሸባሪው ዓላማ የተሰለፉ ሁሉ እጃቸውን በመስጠት ራሳቸውን እንዲያተርፉ፣ የትግራይ ወላጆችም ልጆቻችን የት ደረሱ ብለው እንዲጠይቁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል። “የኢትዮጵያ ፍላጎት ሰላምና ልማት ነው።
ወደዚህ ጦርነት የገባነው ተገድደን ነው። ማሸነፋችን ግን አይቀሬ ነው” ሲሉ የኢትዮጵያን ድል አድራጊነትም ገልጸዋል።