የድሬዳዋ ታክሲ አሽከርካሪዎች ለመከላከያ ሠራዊት ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

15

ድሬዳዋ ኅዳር 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የድሬዳዋ ከ11 ሺህ በላይ የባለ ሶስት እግር የታክሲዎችና ተባባሪ ታክሲዎች አሽከርካሪዎች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ያሰባሰቡትን ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አደረጉ።

የታክሲ አሽከርካሪዎቹ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጎን ሆነው በግንባር ለመሰለፍ ዝግጁ  መሆናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡

የታክሲ አሽከርካሪዎቹ  ተወካይ ወጣት ቃልኪዳን ፀሐይ ድጋፉን ለድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃርና ለሠራዊቱ ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ዛሬ አስረክቧል።

የታክሲ አሽከርካሪዎቹ ቀደም ሲልም ለሀገር መከላከያ ሠራዊት 746 ዩኒት/ከረጢት ደም መለገሳቸውን ወጣት ቃልኪዳን አስታውሷል።

በዛረው የድጋፍ አሰጣጥ ሥነስርዓት ላይ የታክሲ አሽከርካሪዎችና የትራፊክ ፖሊስ አባላት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደም ለግሰዋል፡፡

አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች አልባሳት መሰባሰቡንም ተናግሯል፡፡

የታክሲ አሽከርካሪው ስንታየሁ አራጋው በሥነስርዓቱ ላይ ''የጠቅላይ ሚኒስትራችንን ጥሪ ተከትለን ግንባር በመዝመት ሀገርን ለማዳን ዝግጁ ሆነን እየተጠባበቅን ነው'' ብሏል፡፡

''ገሚሳችን ግንባር እንዘምታለን፣ ገሚሳችን ደግሞ ለአካባቢው ሰላምና ፀጥታ መከበር ከፀጥታ አካላት ጋር ሌት ተቀን እየሰራን እንገኛለን'' ያሉት ደግሞ ሌላው አሽከርካሪ አቶ ሙሉጌታ ረጋሳ ናቸው፡፡

''ለሀገር ሕልውና መስዋዕት እየከፈለ ከሚገኘው መሪ ጎን ተሰልፎ ሀገር ማዳን ዕድለኛነት ነው፤ እኔ ግንባር ዘምቼ ኃላፊነቴን ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ'' ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር የከተማዋ ታክሲ አሽከርካሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት በሀገር ፍቅር ስሜት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የሀገር ሕልውናን ለማረጋገጥ በዘማችነት፣ በገንዘብና ደም በመለገስ፣ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ በመጠበቅ፣ የአሸባሪዎቹን የህወሓትና ሸኔ ተላላኪዎችን ለሕግ በማቅረባቸውም አመስግነዋል፡፡

"እነዚህን ሥራዎች በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ ማከናወን በግንባር የሚካሄደውን የሕልውና ዘመቻ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ያደርገዋልም" ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ በበኩላቸው አሽከርካሪዎቹ ለሀገርና ለአካባቢው ሰላምና ፀጥታ መረጋገጥ ከፀጥታ አካላት ጋር እያደረጉት ያለውን አብነታዊ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም