ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ የህዝቡ ሁለንተናዊ ድጋፍ መጠናከር ይኖርበታል

ጋምቤላ፤ ህዳር 20/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በሚደረገው ጥረት መላው የክልሉ ህዝብ ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚኖርበት የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ አሳሰቡ።
16ኛው የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በጋምቤላ ክልል ደረጃ በጎደሬ ወረዳ   እየተከበረ ነው።

በዓሉ "ወንድማማችነት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በፓናል ውይይት ማክበር በተጀመረበት ሥነ-ሥርዓት ላይ አፈ- ጉባኤዋ እንዳሉት፤አሸባሪው የህወሓት ቡድን የጥፋት ሴራ በመጠንሰስ  ከተላላኪዎችና የውጪ ጠላቶች ጋር አብሮ  ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየጣረ ነው።

ይህንን የአሸባሪው ቡድን የጥፋት ሴራ  ለማክሸፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያቀረቡት ጥሪ በመቀበል የህልውናውን ዘመቻውን መቀላቀል ይገባል ነው ያሉት።

በሀገሪቱ ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በሚደረገው ጥረት መላው የክልሉ ህዝብ እስከ ግንባር በመሄድ ጭምር ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት አፈ-ጉባኤዋ አሳስበዋል።

አሸባሪው ቡድን  እንደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በጋምቤላም ርዝራዥ ተላላኪዎቹ አማካኝነት  ችግር ለመፍጠር ጥረት ቢያደርግም በክልሉ ህዝብ አርቆ አሳቢነት የአካባቢው ሰላሙ ተጠብቆ መቆየቱን ጠቁመው በቀጣይም ይሄው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።

በክልሉ ጎደሬ ወረዳ ዛሬ በፓናል ውይይት ማክበር የተጀመረው 16ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ነገም ቀጥሎ በተጓዳኝም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎች እንዲተገበሩ ለማስቻል  የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶች እንደሚኖሩ ተገልጿል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉን ጨምሮ ሌሎችም  ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ ተዋቂ የሀገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም