ምዕራባዊያኑ በኢትዮጵያ ላይ እየተከተሉት ያለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ምዕራባዊያኑ በኢትዮጵያ ላይ እየተከተሉት ያለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2014 (ኢዜአ) አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ እየተከተሉት ያለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፋ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኙ ላውረንስ ፍሪማን ተናገሩ።
አገራቱ በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ባለው ያልተገባ ጫና እና የሚዲያ ዘመቻ የዓለምን ህዝብ ተሳስተው እያሳሳቱት ይገኛሉ ብለዋል።
በአፍሪካ ጉዳይ ለ30 ዓመታት በኢትዮጵያ ጉዳይ ደግሞ ለ12 ዓመታት ፖለቲካዊ ትንታኔ ምርምር ያደረጉት ላውረንስ ፍሪማን ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብተዋል።
የፖለቲካ ተንታኙ ላውረንስ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አዲስ አበባ የምእራባዊያኑ ሚዲያዎች ከሚያራግቡት በተቃራኒ ሰላማዊና የተለመደ የተረጋጋ እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኗን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ፍፁም ሰላምና የተረጋጋች ሆና ሳለ በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኢምባሲ የሚያወጣው መረጃም ከእውነታው የራቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ አገራት ዜጎቻቸው ከአዲስ አበባ እንዲወጡ የሚወተውቱበት ሁኔታም ፍርሃት ለማሳደር ያለመ እንጂ እውነታው ሌላ መሆኑን ይናገራሉ።
"ኢትዮጵያ በቀላሉ የምትበታተን አፍጋኒስታን አይደለችም" ያሉት ፍሪማን፤ የአሜሪካ መንግስትና አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ እየተከተሉት ያለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፋ መሆኑን ገልጸዋል።
የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ እያራመደ ያለው አቋም የተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መሆኑንም ጠቅሰው አሸባሪ ሃይልን መደገፏና ኢትዮጵያን ከአጎዋ ማገዷ ፍፁም ስህተት መሆኑን ገልጸዋል።
በሕዝብ ተሳትፎ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት ላይ እንዲህ አይነት ያልተገባ ጫና እና ዘመቻ መክፈት ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም አብራርተዋል።
አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ ለምን ይህን ያህል ጫና አበረቱ በሚለው ጉዳይ ላይ ሲያብራሩም ከሕወሃት ጋር የነበራቸው የረጂም ጊዜ ወዳጅነትና የዜሮ ድምር ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
የወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት ከቁጥጥራችን ውጭ ይሆናል በሚል ስጋት የአፍሪካን ቀንድ የትርምስ ቀጠና ለማድረግ ያለመ ፖሊሲ እየተከተሉ ስለመሆኑም ላውረንስ ፍሪማን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት በቁርጠኝነት እየሰራች ያለች አገር መሆኑን ገልጸው፤ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ አቋም በማራመድ አካባቢውን ከማተራመስ ይልቅ በልማት የማገዝ ፖሊሲን እንድትከተል ጠይቀዋል።