ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ተጫዋቾች ለመከላከያ ሰራዊት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ለመስጠት ቃል ገቡ

ህዳር 20/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ክለብ ተጫዋቾች ለመከላከያ ሰራዊት 40 ሚሊዮን ብር በላይ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

የሊጉ ተጫዋቾች ለአገር መከላከያ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ቦርድ በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው።

የ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እና የኢትዮጵያ ቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ በሐዋሳ ከ16ቱም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጋር ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ በሚደረግበት ሂደት ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ የገንዘብ ድጋፉ ይደረጋል ተብሏል።

የፕሪሚየር ሊጉ ተጫዋቾች እንኳን እግር ኳስ መጫወት በሰላም ወቶ መግባት የሚቻለው ሀገር ስትኖር ነው በማለት የአንድ ወር ደሞዛቸውን ሀገርን ከመፍረስ ለመታደግ በዱር በገደሉ የህይወት መስዋትነትን እየከፈለ ላለው ለሀገር መከላከያ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

ይህንን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ከገቡት ተጫዋቾች መካከል የሌሎችአፍሪካውያን ተጫዋቾችም ''ይህ እኛንም ይመለከታል ''በማለት ድጋፍ ለማድረግ ወስነዋል።

እንደ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ የክለቦቹ አመራሮችም፤ይህን ድጋፍ በደጋፊ ማህበራትም በኩል ተጠናክሮ በደም ልገሳ ለማስቀጠል ቃል ገብተዋል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም