ቀጥታ፡

በተሰማራንበት ዘርፍ ጠንክረን በመሰራት የህልውና ዘመቻውን እንደግፋለን

እንጅባራ ኅዳር 20 /2014(ኢዜአ) ጠንክረው በመስራት የህልውና ዘመቻውን  የሚደግፉ መሆኑን በእንጅባራ ከተማ በተለያዩ ሙያ ዘርፎች የተሰማሩ የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ይገልጻሉ ።
 አቶ በቃሉ ግርማ በከተማዋ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ድርጅት ባለቤት ሲሆኑ  የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ግንባር መዝመት ኢትዮጵያ የተከፈተባትን ጦርነትን በድል እንድትወጣ ያደርጋል ብለዋል።

በተሰማሩበት  ዘርፍ  ጠንክረው በመስራት የህልውና ዘመቻውን ለመደገፍ  ይበልጥ መነሳሳታቸውን ይናገራሉ።

የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስከበር ደጀን በመሆንም የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ  አስታውቀዋል።

''እስከዛሬ የሰራሁት ወደፊትም የምሰራው የኢትዮጵያ ክብሯ ሲጠበቅ ነው'' ያሉትአቶ በቃሉ፤ ለዘመቻው እስካሁን 3 ሺህ ብር ሰጥቻለሁ፤ ወደፊትም እየሰራሁ እቀጥላለሁ'' ነው ያሉት።

በቀርከሃ ምርት የተሰማራው ወጣት አዲሱ በላይ፤  የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን ተባብረው ኢትዮጵያን እየወጉ ባሉበት ወቅት የምሰራው እኔን ወክለው እየተዋጉ ላሉት ደጀን ለመሆን ነው ብሏል።

''በሥራዬ ከማገኘው ትርፍም ከጠላት ጋር እየተፋለመ ላለው ሠራዊት የማካፍለው ይሆናል''ሲል ይገልጻል።

የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ሳይጠፉ ''ዕድገቴ ስለማይረጋገጥ እስከ ድሉ መጨረሻ ሠራዊቱን እደግፋለሁ'' ብሏል ወጣት አዲሱ።

ኢትዮጵያን ለማዳን በግንባር ከጠላት ጋር እየተፋለመ ላለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ደጀን በመሆን ያለመታከት  እንደሚደግፉ  የተናገሩት ደግሞ በከተማዋ የእንጨትና የቢሮ ዕቃዎች ሥራ ድርጅት ባለቤት የሆኑት አቶ ተሻለ የኔው ናቸው።

''ግንባር ከተሰለፈው ሰራዊት እየተሰማ ያለው የድል ዜና የሥራ ተነሳሽነቴን ጨምሯል'' ያሉት አቶ ተሻለ፤ ውጤታማ ሥራ በማከናወን ሠራዊቱን ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

በዚህ ወቅት ግንባር ወይም ሥራ ላይ የሌሉ ዜጎችም ለሀገር ሰላምና ደህንነት ስጋትና ሸክም ከመሆን ወጥተው ሀገራቸው በምትፈልገው መስኮች በመሰማራት ከታሪክ ተወቃሽነት እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የብረታብረት ማምረቻ ድርጅት ባለቤት አቶ ትዕዛዙ ካሣሁን በበኩላቸው ፤ ሀገርን ከጠላት ለመታደግ በግንባር የተሰለፈው የመከላከያ ሰራዊት ከድርጅታቸው ከሚያገኙት ገቢ በመቀነስ ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የህልውና ዘመቻው በድል እስከሚጠናቀቅ ሠራዊቱን በመደገፍ ኢትዮጵያን ለማዳን  የድርሻቸውን እንደሚወጡ ነው ያመለከቱት።

በኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች  ጠላት በየደረሰበት እየተደመሰሰ እየተመዘገበ ያለው ድልም በሙያቸው በርትተው ለመሥራት እንዳነሳሳቸው  ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም