ዲፕሎማቶችና የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የምዕራባዊያንን ጣልቃ ገብነት ሊታገሉ ይገባል- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ዲፕሎማቶችና የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የምዕራባዊያንን ጣልቃ ገብነት ሊታገሉ ይገባል- ምሁራን
ሰመራ ህዳር 20 /2014 (ኢዜአ) አፍሪካዊያን ዲፕሎማቶችና የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ምዕራባውያን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ-ገብነት መታገል ይገባቸዋል ሲሉ የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
ምእራባዊያኑ ከኢትዮጵያ አልፎ በጥቁር ህዝቦች ላይ ለመጫን የሚፈልጉትን ዘመናዊ ቅኝ-አገዛዝ በተባበረ ክንድ ማክሸፍ እንደሚገባ ምሁራኑ ለኢዜአ አስታውቀዋል።
የዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር አቶ ኑሩ መኩሪያ እንዳሉት ከአሸባሪው ህወሀት ሀገር የማፍረስ ተግባር ጀርባ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሆኑ የውጭ ሀይሎች እጅ አለበት።
ምዕራባውያን ከእነሱ ፍቃድና ተጽዕኖ ነጻ ሆኖ የሀገሩን ህዝብና ፍላጎት የሚያስቀድም መንግስትና የኢኮኖሚና የፖለቲካ ነጻነት ያለው ሀገር በአፍሪካ እንዳይኖር ሌት ተቀን እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያለው ገደብ አልባ ጣልቃ-ገብነት ለሀገራችን ወቅታዊ ፓለቲካዊ ቀውስ ሁነኛ አፍሪካዊ መፍትሄን እንደማይሹ አመልክተዋል።
ምእራባዊያኑ በመገናኛ ብዙሀኖቻቸው ጭምር ታግዘው የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ችግሩን የበለጠ ለማወሳሰብ እያደረጉ ያለው ሙከራ የእኩይ ሴራቸው ሌላው ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
"ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ በዴሞክራሲና ሰብአዊነት ስም እየፈጸሙ ያለውን ግልጽ ፓለቲካዊ ሸፍጥ በመታገልና በማጋለጥ በኩል አጋርነታቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል" ብለዋል።
መንግስትም አዲስ አበባ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መቀመጫ መሆኗን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ተከታታይነት ያላቸው የዲፕሎማሲ ሥራዎችን መስራት እንዳለበት መምህሩ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያን አውነታ ለማሳወቅ እንግሊዘኛና አረብኛ ቋንቋን ተጠቅመው መረጃ የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙሀንን በስፋት መጠቀም እንደሚገባ ምሁሩ ጠቁመዋል።
ምዕራባዊያን በአፍሪካ ሀገራት ላይ የሚያራምዱት ፓሊሲ አዛዥ-ታዛዥነት የተጠናወተው ከቀኝ ገዢነት ቅኝት ያልተላቀቀ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የሲቪክስና ስነዜጋ መምህሩ አቶ ሙስታር ጠይብ ናቸው።
ፖሊሲያቸው ሀገራት እውነተኛ ዴሞክራሲም ሆነ የተፈጥሮ ሃብታቸውን አልምተው የህዝባቸውን ኑሮ በሚፈለገው ደረጃ እንዳያሻሽሉ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን አመልክተዋል።
መምህሩ እንዳሉት አሜሪካንን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባዊያን ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ እያራመዱ ያለው ፓሊሲ ኢትዮጵያ ለዘመናት ከውስጥና ከውጭ ሃይሎች የሚገጥማትን ችግር በራሷ አቅም በመፍታት በሉአላዊነቷና ክብሯ የማትደራደር ጠንካራ ሀገር እንደሆነች የዘነጋ ነው።
"ይህ ካልሆነም በቀጥታ የሞከሩት የቅኝ ግዛት ፍላጎታቸው የከሸፈባቸው ሃይሎች ዛሬ የገጠመንን ችግር እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የሸረቡት ሴራ ነው" ብለዋል
"በመሆኑ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር እየተፋለምን ያለነው ግዛታዊ አንድነታችንን ለማስከበር ብቻም ሳይሆን እሱን ሽፍን እድርገው ሀገራችንን በእጅ አዙር የሚወጉትን የውጭ ሃይሎችንም ጭምር በመሆኑ ትግሉ ዳግማዊ አድዋ ሊባል የሚችል የነጻነትና የሉአላዊነት ትግል ነው" ሲሉም አክለዋል።
እንደ መምህሩ ገለጻ ጦርነቱ በአፍሪካና በጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት በሆነችው ኢትዮጵያና የቀኝ ገዢነት መንፈስ በተጠናወታቸው ሃይሎች በመሆኑ አጀንዳው የአፍሪካዊያንና የመላው ጥቁር ህዝቦች የነጻነት ጥያቄ ጭምር መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል።
የዩኒቨርሲቲው የህዝብ ግንኙነት ትምህርት መምህር አቶ ሃቢብ መሀመድ በበኩላቸው ምእራባዊያን እራሳቸውን ቅዱስ አስመስለው በተለይም አፍሪካዊያን ችግር ሲገጥማቸው በራሳቸው አቅም በሰላም እንዲፈቱ ከመደገፍ ይልቅ ለፓለቲካዊ ትርፍ ሲሯሯጡ መመልከት የተለመደ መሆኑን ተናግረዋል።
"አንዳንድ ሀገራት በኢትዮጵያም በህጋዊ መንገድ ከተመረጠ መንገስት ይልቅ በሃይል ስልጣን እይዛለሁ ብሎ ጦር ከመዘዘ አሸባሪ ጎን ሆነው በሀገራችንና ህዝባችን ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ሸፍጥ እየሰሩ ይገኛሉ" ብለዋል።
ምዕራባዊያን በሰብአዊ እርዳታ ስም ለሽብር ቡድኑ እንቅስቃሴ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ የችግሩ የመፍትሄው አካል ከመሆን ይልቅ በህዝባችን ላይ በቡድኑ እየደረሰ ላለው መከራ የማይናቅ ድርሻ እንዳላቸውም ገልጸዋል።
እውነቱ የገባቸው አንዳንድ አፍሪካዊያን ዲፕሎማቶችና የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች የኢትዮጵያን እውነት በማሳወቅ አጋርነታቸውን እያሳዩ መሆናቸውን ጠቁመው ተግባራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አመላክተዋል።
አፍሪካዊያን ዲፕሎማቶችና የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለጥቁር ህዝቦች የነጻነት ቀንዲል ከሆነችው ኢትዮጵያ ጎን በመቆም ታሪካዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።