ቀጥታ፡

ጦርነቱን በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ በአንድነትና በመደማመጥ ለድል መነሳት ይገባል

እንጅባራ፤ ህዳር 19/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድንና ተባባሪዎቹ በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን ጦርነት በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ በአንድነትና በመደማመጥ ለድል መነሳት እንደሚገባ ተመለከተ።

በወቅታዊ ክልላዊና ሀገራዊ ጉዳይ ላይ የሚመክር ህዝባዊ መድረክ በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ-ሠላም ከተማ ተካሂዷል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የሠላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም እንዳሉት፤አሸባሪው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን ለመውጋት የተነሳው ብቻውን ሳይሆን የኢትዮጵያን ጠላቶች ድጋፍ አስቦ ነው።

"የወራሪው ባንዳ ዓላማ ህዝብን ማሰቃየት፣ ንብረት ማውደምና መዝረፍ ብቻ ሳይሆን ሀገርን አፍርሶ ለውጭ ጠላት አሳልፎ መስጠትና አቅም የሌላት ኢትዮጵያን ማየት ነው" ብለዋል።

ህዝቡ በዚህ ወቅት መደማመጥ፣ ወደ ግንባር መዝመት፣ ሰልጥኖ ራስን ማዘጋጀት፣ አካባቢውን መጠበቅ እና የዘማች ቤተሰብን በመንከባከብ ለዘመቻው የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ግንባር መዝመት የማይችሉ አባቶች ወጣቱ ግንባር ዘምቶ ታሪካዊ አደራውን እንዲወጣ መቀስቀስ እንዳለባቸው የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ሀገር ለማፍረስ የተነሱትን ጠላቶች በመደራጀት መመከት እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።

አሸባሪው የህወሓት ቡድንና ተባባሪዎቹ በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን ጦርነት በአሸናፊነት በማጠናቀቅ በአንድነት ለድል መነሳት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው፤ የሽብር ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በንጹሀን ላይ ያልፈፀመው ግፍና መከራ እንደሌለ አውስተዋል።

"የሀገርና የህዝብን ህልውናን በማስጠበቅ ኢትዮጵያን ከመፍረስ አደጋ መታደግ የሚቻለው በአንድነት ሆነን የድርሻችንን ስንወጣ ነው" ብለዋል።

ወራሪው በእምነት ተቋማት ላይ ጭምር ጥፋት እየፈጸመ በመሆኑ ወጣቱ ሀገሩንና ሃይማኖቱን እንዲጠብቅ የሀይማኖት አባቶች የድርሻቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

"በሃገር ውስጥና በውጭ ሃይሎች በተቀናጀ አግባብ የተከፈተብንን ጦርነት በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ ሁላችንም የተግባር ሰው በመሆን ደጀንነታችንን ልናጠናክር ይገባል" ነው ያሉት ዶክተር ይናገር።

ወቅቱ አንዱ ሌላውን ቁጭ ብሎ የሚተችበት ሳይሆን ሁሉም በአንድነት ለህልውና ዘመቻው ስኬት የሚተጋበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ እንደሆነም አመላክተዋል።

እንደ ህዝብም ሆነ እንደ ሃገር የተደቀነብንን አደጋ  በአንድነት የምንመክትበት ወሳኝ ወቅት ላይ  ነን ያሉት ደግሞ  የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መልካሙ ተሾመ ናቸው።

የሀገሪቱ  የወደፊት ህልውና ለማረጋገጥ በፈቃደኝነት ወደ መከላከያና ልዩ ኃይል መቀላቀል እንደሚገባ ጠቁመው፤ አካባቢን ከሰርጎ ገቦች መጠበቅም እንዲሁ።  

በህልውና ዘመቻው ለመሳተፍ የፀና ፍላጎት ቢኖራቸውም በዕድሜ ምክንያት ሊሳተፉ ባለመቻላቸው የ11ኛ ክፍል ተማሪ ልጃቸውን መከላከያን እንዲቀላቀል እንደላኩ የገለጹት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊ አቶ መንበር መላኩ ናቸው።

"የተማረው አካል የውጭ ጫናውን ይከላከልልን፤ የሀገር ውስጥ ተላላኪና ባንዳውን እኛው ተደራጅተን እንጠብቃለን" ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም በአካባቢያቸው ለሠራዊቱ የተጠናከረ ደጀን ከመሆን ባለፈ የዘማች ቤተሰቦችን የመንከባከብ ግዴታቸውን እንደሚወጡ ነው የገለጹት።

በምክክር መድረኩ የፌደራልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች የከተማዋ ነዋሪዎችና የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች መሳተፋቸውን ከእንጅባራ ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም