የመገናኛ ብዙኃን ከተፅዕኖ ነጻ ለማድረግ የወጡ የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻል ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የመገናኛ ብዙኃን ከተፅዕኖ ነጻ ለማድረግ የወጡ የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻል ያስፈልጋል
አዲስ አበባ ነሀሴ 16/2010 በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ ለማስወገድና ሚዛናዊ የሆነ መረጃ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የወጡ የህግ ማዕቀፎች ሊስተካከሉ እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ። በዘርፉ የሚታዩ የህግ ክፍተቶችን ለማሻሻል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር የፖሊሲ ጥናት አካሂዷል። የሚዲያ ፎረም አባላት በተገኙበት በተካሄደው ውይይት እንደተጠቀሰው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት ትልቁ ፈተና ተገቢ የሆነ የህግ ማዕቀፍ አለመኖር መሆኑ ተገልጿል። በዚህም የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በመንግስት ተፅዕኖ ስር ወድቀው በሚፈለገው ደረጃ ለኅብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ ሳያዳርሱ ቆይተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህርና የጥናት ቡድኑ አባል አቶ ቴዎድሮስ ውድነህ እንዳሉት፤ የመገናኛ ብዙኃን ሚዛናዊ መረጃ ተደራሽ እንዳያደርጉ የወጡ የህግ ማዕቀፎች ተፅዕኖ እያሳደሩ ነው። መንግስት የህጉን ክፍተት በመጠቀም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ እንዳያሰራጩ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል። በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህር ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ በበኩላቸው በመገናኛ ብዙኃን ላይ ያለው የህግ ማዕቀፍ ተቋማቱ በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ ትልቅ እንቅፋት የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል። በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በጋዜጠኝነት የሰራው ጋዜጠኛ እሸቱ ገለቱ እንዳለው፤ ከህግ ማዕቀፍ ጀምሮ እስከ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ድረስ ክፍተት አለ። የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ለጋዜጠኞች ከሚሰጠው ሙያዊ ነጻነት ይልቅ አሳሪ አንቀፆች ያሉበት መሆኑን ገልጿል። በመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ላይ የወጡ የህግ ማዕቀፎች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል። የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው በመንግስት ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የሚዲያ ፖሊሲ ማሻሻያ ጥናት አንዱ ሲሆን ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ ባለሙያዎች በህግ ማዕቀፉ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች እንዲጠኑ መደረጉን ገልጸዋል። የቀረበው የፖሊሲ ጥናት ከተሳታፊዎቹ በሚገኝ ግብዓት ከዳበረ በኋላ ለመንግስት ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።