ምዕራባዊያን ኢትዮጵያ ችግር በገጠማት ጊዜ ሁሉ ወደ ገደል ሲገፏት ኖረዋል - ኢዜአ አማርኛ
ምዕራባዊያን ኢትዮጵያ ችግር በገጠማት ጊዜ ሁሉ ወደ ገደል ሲገፏት ኖረዋል
አዲስ አበባ፣ ህዳር 18/2014(ኢዜአ) ምዕራባዊያን ኢትዮጵያ ችግር በገጠማት የታሪክ አጋጣሚ ሁሉ ከችግር ለማውጣት ሳይሆን ወደ ችግር አፋፍ ሲገፏት ኖረዋል ይላሉ አምባሳደር ጥሩነህ ዜና።
ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ በዲፕሎማሲው መስክ ኢትዮጵያን ያገለገሉት አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ በብዙ የዲፕሎማት መስኮች በነበራቸው ሙያ ምዕራባዊያን አገራትን በቅርበት የማየት ዕድል ነበራቸው።
ከኢዜአ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ቆይታ ያደረጉት አምባሳደሩ ምዕራባዊያን በየዘመኑ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና አመክንዮን በዋናነት ከአድዋ ድል ጋር አያይዘው ያብራራሉ።
ይኸውም በአውሮፓዊያኑ 1884 የበርሊን አፍሪካን የመቀራመት ጉባዔ በኋላ ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛትን ድል አድርጋ የአፍሪካዊያን የነጻነት ትዕምርት መሆኗ በክፉ ዓይናቸው እንዲመለከቷት ሰበብ መሆኑ ነው።
ድሕረ አድዋ ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ምልክት ሆና መቀጠሏ፤ የጥቁር አፍሪካዊያን ታሪክና ስልጣኔ ቅርስ መሆኗም ለነጮች መጥፎ ስሜት እንዲያድርባቸው አድርጓል ባይ ናቸው።
በዚህም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ደካማ በመሆኗ ከምዕራባዊያን ጋር ግንኙነት ቢኖሯትም ዳሩ ችግር በገጠማት ወቅት አንድም ጊዜ ከጎኗ አልተሰለፉም፤ በተቃራኒዋ ቆመዋል እንጂ ብለዋል አምባሳደር ጥሩነህ።
ለአብነትም በ1928ቱን የፋሺስት ኢጣሊያ የግፍ ወረራ የመንግስታቱ ማኅበር ማስቆም አለመቻሉ፣ የራሷ ጦር መሳሪያ ከምታመርተው ኢጣሊያ ጋር እኩል ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ መጣላቸው ብሎም በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መንገድ መሳሪያ እንዳታጓጉዝ መከልከላቸውን ይጠቅሳሉ።
በሶማሊያ ወረራ ወቅትም ለኢትዮጵያ ወዳጅ አገር የምትባለዋ አሜሪካ የግፍ ወረራ ሲፈጸምባት ክፍያ የፈጸመችበትን የጦር መሳሪያ ከመከልከል ባለፈ ከታሪካዊ ጠላቶች በመወገን ኢትዮጵያ መክዳቷን ያወሳሉ።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እና ለቀይ ባሕር ስትራቴጂክ ስፍራ ያላት መልክዓ ምድራዊ አቀማምጥ ለምዕራባዊያን ስጋት ትሆናለች በሚል እንድትዳከምና እንድትፈራርስ የምንጊዜም ፍላጎታቸው ነው ይላሉ።
እነዚህ ኢትዮጵያ ችግር በገጠማት ጊዜ ሁሉ ወደ ገደል ሲገፏት የነበሩ ምዕራባዊያን ዛሬም በገጠማት የሕልውና አደጋ አሜሪካን ጨምሮ ከአሸባሪው ቡድን ጋር መወገናቸው ህወሓትን ወደውት ሳይሆን ኢትዮጵያን ለመበታተን ሊጠቀሙበት ስለፈለጉ ነው ብለዋል።
ምዕራባዊያኑ ከትናንት እስከ ዛሬ ኢትዮጵያን ለመበታተን ሲሰሩ እንደቆዩት ሁሉ ነገም ምቹ ጊዜ እየጠበቁ ኢትዮጵያን ለመበታተን ከመሞከር አይቦዝኑም ብለዋል።
ለዚህ መፍትሄው ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል የመገንባት፣ ውስጣዊ አገራዊ ስሜት የመፍጠር እና የኢኮኖሚ አቅምን የማጠናከር እርምጃዎች እንደሚያስፈልጉ አመልክተዋል።
በኢኮኖሚ ረገድም ቢያንስ የምግብ ፍጆታ በአገር ውስጥ ምርት መሸፈን እንዲሁም የግብርና መሳሪያዎች ከሺህ ዘመናት ከነበረው ኋላቀር ስርዓት መላቀቅ እንዳለባቸው መክረዋል።
የኢኮኖሚ ጥገኝነት እያለ የፖለቲካ ነጻነትን ማረጋገጥ እንደማይቻል የገለጹት አምባሳደር ጥሩነህ፤ ከግብርና ግብዓቶች ግዥ እና ከልመና መውጣት ያሻል ብለዋል።
ከ40 ዓመታት በፊት የአርሶ አደሩን ኑሮ ለመለወጥ የነበሩ ሙከራዎች እንዳልቀጠሉ አስታውሰው፤ ዛሬ የትምህርት ተቋማት በተስፋፉበት 80 በመቶ የሚሆነውን ሕዝብ ኑሮ ሊለወጥ ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሕልውና እስካሁን ተጠብቆ የቆየው ሕዝቡ ጠንካራ ብሔራዊ ስሜት ስላለው ነው ያሉት አምባሳደር ጥሩነህ፤ ነገር ግን የትውልዱ አገራዊ ስሜት ከጊዜ ጊዜ እየተሸረሸረ መምጣቱን አንስተዋል።
ለዚህም ብሔራዊ ስሜትና ውስጣዊ አንድነትን የሚያጠናክር የትውልድ ግንባታ ያስፈልጋል ነው ያሉት።