የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

63

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17/2014 (ኢዜአ) የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

ድጋፍ ካደረጉት ግለሰቦች መካከል ወይዘሮ ቦጋለች ከበደ ቤታቸውን ሸጠው 2 ሚሊዮን ብር ሲለግሱ አርቲስት ደበበ እሸቱም 25 ሺህ ብር ለግሷል።

ለሰራዊቱ ያደረግነው ድጋፍ አብሮነትና አጋዥነታችንን ለማሳየት ነው ብለዋል ለጋሾቹ።

በአሜሪካ የሚኖሩት የአቶ ደረጀ አሰፋ ቤተሰቦች 120 ሺህ ብር፣ የጥንታዊት የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር 500 ሺህ ብር፣ ጤና ሚኒስቴር 31 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ከአሁን በፊት የገጠማትን ፈተና በድል የመወጣት ልምድ ስላላት አሁንም ታሸንፋለች ብለዋል የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ።

የጥንታዊት የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበኩላቸው ማህበሩ ለኢትዮጵያ የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ 5 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ ቤቶች ኮርፖሬሽን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮ ቴሌኮም ደቡብ አዲስ አበባ ዞን የጥበቃ ሰራተኞች 226 ሺህ ብር የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ፤ ሁሉም ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው ኢትዮጵያዊነት የማይበጠስ ገመድ በመሆኑ በተባበረ ክንድ ጠላቶቻችንን እናሸንፋለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም