ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሠላም እስከሚረጋገጥ ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ ህዳር  17/2014 (ኢዜአ) የግንባታ ስራ ተቋራጮች የሕልውና ማስከበር ዘመቻውን የሚደግፍ የሎጂስቲክስ ድጋፍ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ገለጹ።

የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማኅበር ጋር በመተባበር የሕልውና ዘመቻውን በሁለንተናዊ መልኩ ለማገዝ የሚረዳ የንቅናቄና የድጋፍ መድረክ አካሂዷል።

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግርማ ኃብተማርያም ማኅበሩ የሕልውና ማስከበሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለመከላከያና ለሕዝባዊ ሠራዊቶች የገንዘብና የሎጂስቲክስ ድጋፎች ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ድጋፉ የተፈናቀሉ ወገኖችን መርዳትን ያካተተ መሆኑንም በመጠቆም።

ተቋራጮች ለሕልውና ዘመቻው የሚያደርጉትን ድጋፍ የበለጠ ለማስተባበር ሁለት አብይ ኮሚቴዎች በማቋቋም  እየሰሩ መሆኑንና ድጋፋቸውም አገር ሠላም እስከምትሆን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የማኅበሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ ኢትዮጵያ ችግር ገጥሟት ልጆቿን በጠራችበት ጊዜ ሁሉ ሕዝቦቿ አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በአድዋና በሌሎች የጦር ሜዳ ውሎ ድሎች አባቶቻችን ነፃ አገርና ኩሩ ሕዝብ አስረክበውናል ያሉት ኢንጂነር ዘለቀ የአሁኑ ትውልድም ነፃና ኩሩ ትውልድ ለመፍጠር የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የስራ ተቋራጮች ከዚህ ቀደም ሲያደርጉ ከቆዩት ድጋፍ በተጨማሪ በቀጣይም ለሕልውና ዘመቻውና ለተፈናቃዮች ድጋፍ ለማድረግ የሚያግዙ እንደ ተሽከርካሪ፣ ስካቫተር እና ሎቤድ የመሳሰሉ የግንባታ መሳሪያዎቻቸውን እንደሚደግፉ ገልፀዋል።

በቀጣይም የዘማች ቤተሰቦችን የመደገፍ ተግባራት እንደሚከናወኑ አክለዋል።

የማኅበሩ አባል ኢንጂነር ሰለሞን አለማየሁ እንደገለጹትም ግለሰባዊና ቡድናዊ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አገራዊ ፍላጎትን በመፃረር የከፈቱት ጦርነት ወደ አስገዳጅ የሕልውና ማስከበር ዘመቻ አስገብቶናል ብለዋል።

አገራዊ ፍላጎት ማበብ የሚችለው ሁሉም ዜጋ ዋጋ በመክፈል ከትሩፋቱ ሲቋደስ ብቻ በመሆኑ ትግሉ ለራስና ለአገር መሆኑን በመረዳት በግንባር ቀደምትነት መሰለፍ አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

ለሕልውና ዘመቻው በድል መጠናቀቅ ካደረጉት ቁሳዊ ድጋፍ ባሻገር እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ ኢንጂነር ገዛኸኝ ተካ ናቸው።

የስራ ተቋራጮቹ በደም ልገሳና የአካባቢያቸውን ሠላም በማስጠበቅ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አያልነሽ ኃብተማርያም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የግንባታ ተቋራጮች ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ ደጀንነታቸውን ማሳየት ይገባቸዋል ብለዋል።

ቢሮው ከዚህ ቀደም ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማሰባሰቡንም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም