አፍሪካዊያን እንደፓን አፍሪካኒዝም ተጋድሎ ከኢትዮጵያ ጎን በመሰለፍ ድምጻቸውን ማሰማት ይጠበቅባቸዋል-ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካዊያን እንደፓን አፍሪካኒዝም ተጋድሎ ከኢትዮጵያ ጎን በመሰለፍ ድምጻቸውን ማሰማት ይጠበቅባቸዋል-ምሁራን
አርባ ምንጭ ህዳር 17/2014(ኢዜአ) መልኩን ቀይሮ የመጣውን የምዕራባውያን ዘመናዊ የቅኝ አገዛዝ አካሄድ ለማስቆም አፍሪካዊያን እንደፓን አፍሪካኒዝም ተጋድሎ ሁሉ ከኢትዮጵያ ጎን በመሰለፍ ድምጻቸውን ማሰማት ይጠበቅባቸዋል ይላሉ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፡፡
በየጊዜው ሊቀራመቷት የመጡትን ወራሪ ጠላቶች በጀግኖች ልጆቿ መክታና አሳፍራ የመለሰች ከራሷም ባለፈ ለአፍሪካውያን የነጻነትን ጎህ የቀደደች ሀገር ናት - ኢትዮጵያ።
ጀግኖች አባቶችና እናቶች በከፈሉት መስዋዕትና ኢትዮጵያ ለማንም ቅኝ ተገዥ ሳትሆን በመኖሯ ዛሬ ድረስ ልጆቿ በየደረሱባቸው የዓለም ዳርቻ አንገታቸውን ቀና አድርገው ይሄዳሉ።
የአፍሪካ ሕብረትን መስራችና ለሕብረቱ መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካኒዚም ተጋድሎ ከፍተኛ ስፍራ ያላት የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ምሳሌም ሆና ትጠቀሳለች
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ሙልጌታ ደበሌ እንደሚሉት፤ በፓን አፍሪካኒዚም ተጋድሎ ኢትዮጵያ ባላት ጉልህ ቦታ መላው የጥቁር ህዝብ ዛሬ ድረስ የነጻነው ቀንዲል አድርጎ ያያታል።
እኔ የማልመራት ኢትዮጵያን ሲኦልም ቢሆን ገብቼ አፈርሳታለው ብሎ የተነሳው አሸባሪው ህወሓት ለ27 ዓመታት የቦጠቦጣት ሳይበቃው የህዝቦቿን አንድነት በዘርና ሃይማኖት እከፋፍላለሁ በሚል ዛሬም ለታሪካዊ ጠላቶቿ አሳልፎ ለመስጠት ቆርጦ ተነስቷል።
ዶክተር ሙሉጌታ እንዳመለከቱት፤ አሸባሪው ህወሓት በመንግስት የቀረበለትን አብሮ የመስራትና የሰላም አማራጭ ባለመቀበል በመከላከያ ሠራዊቱ የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመፈጸም ኢትዮጵያን በይፋ መውጋት ጀምሯል።
ግቡን ኢትዮጵያን በማፍረስ ለውጭ ጠላቶቿ አሳልፎ መስጠት ያደረገው አሸባሪና ባንዳው ቡድን በወራራ በያዛቸው የአማራና አፋር አካባቢዎች በንጹሀንና በሀገር ሀብት ላይ ታሪክ የማይረሳው ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም አውስተዋል።
ቡድኑ ንጹሀንን በግፍ እየጨፈጨፈና የህገር ሀብት እያወደመ ምዕራባዊያን ወገንተኛ ሆነው በመገናኛ ብዙሀኖቻቸው ጭምር ኢትዮጵያ ላይ በሀሰት ዘምተዋል።
ጥረታቸው ኢትዮጵያን አጣብቂኝ ውስጥ በመክተት ነጻነቷና ክብሯ ተጠብቆ የኖረች ኢትዮጵያን በእጅ አዙር በቁጥጥራቸው ስር ለማዋል መሆኑን ዶክተር ሙሉጌታ ይገልጻሉ።
ምዕራባውያን ለራሳቸው ጥቅምና የበላይነት ሲሉ በአፍሪካ ጠንካራ መንግስታት እንዲፈጠር አይፈልጉም።
አሸባሪውን ህወሓት በመደገፍ በኢትዮጵያ ላይ የተለያየ ጫና እያደረጉት ያለበት ምክንያት ለእዚህ መሆኑን ያመለከቱት ምሁሩ፤"የአፍሪካዊን እንደፓን አፍሪካኒዝም ተጋድሎ ሁሉ ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፈው የበኩላቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
የህልውና ዘመቻው ፈጥኖ እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ህዝብ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠልና በተሠማራበት የስራ መስክ ውጤታማ መሆን እንዳላበትም ጠቁመዋል።
ሌላው በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል አስተባባሪ ጎድሰንድ ኮኖፋ በበኩላቸው፤ ዘመኑ እንደ ቅኝ ግዛት ዘመን አፍሪካውያንን በፈለጉት መንገድ ለመምራት የሚቻልበት ጊዜ አይደለም ይላሉ።
"በአፍሪካ ውስጥ የበላይነትን ለማግኘት ሲባል በአፍሪካ ሀገራት አሻንጉሊት መንግስት ለማስቀመጥ የሚደረገውን የምዕራባውያንን ሩጫ ለማስቆም መላው አፍሪካዊ በጋራ መነሳት ይኖርበታል" ብለዋል።
በአፍሪካ የነጻነት ምሳሌ የሆችው ኢትዮጵን እጅ በመጠምዘዝ ዘመናዊ እቅኝ ግዛት ለማምጣት የሚደረገውን ሴራ አፍሪካውያን ተረድተው ከኢትዮጵያ ጋር መቆም እንዳለባቸው አመልክተዋል።
"ኢትዮጵያ ፀረ ምዕራባዊ አቋም የላትም" ያሉት ምሁሩ፤ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ በህዝብ የተመረጠን ህጋዊ መንግስት ለመጣል ሽብርተኛን መደገፍ ህዝብን መናቅ መሆኑንም ገልጸዋል።
ምዕራባውያን በሰላምና በዴሞክራሲ ስም የራሳቸውን ፍላጎት እንደሚያራምዱም ነው ምሁሩ ያመለከቱት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደግንባር መዝመት በህዝቡ ላይ ትልቅ መነሳሳት መፍጠሩን በማውሳት አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህር ያምራል መኮንን ናቸው።
ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሰረት የጣለች ሀገር መሆኗን አስታውሰው፤ "የምዕራባውያን ዘመቻ ኢትዮጵያን በማፍረስ አፍሪካውያንን አንገት ማስደፋት" ብለዋል
ይህ የምራባዊያን ፍላጎት እንዳይሳካም መላው አፍሪካዊ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ተቃውሞውን ማሰማት እንዳለበት አመልክተዋል።
ከአፍሪካ ወንድሞቻችን ከነጆሞ ኬኒያታ፣ ከነጁሊየስ ኔሬሪ፣ ከንዋሚ ንኩሩማን፣ ከነገማል አብዱልናስር ጋር ለአፍሪካ አንድነት መመስረት ኢትዮጵያ ደማቅና የማይፋቅ አሻራ አስቀምጣለች ብለዋል ምሁሩ ።
"አፍሪካዊያን ከኢትዮጵያ ጎን መቆም ያለባቸው ጊዜው አሁን ነው፤ ኢትዮጵያን መደገፍ ከሞራል፣ ከህግና ከታሪክ አንፃር ተገቢነት ያለው በመሆኑ በአንድነት ድምጻቸውን ማስማት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ይህ ትግል የመላ ጥቁር ሕዝቦች ነው፤ ኢትዮጵያ አንበርክኮ ጥቁር ሕዝብን ለማሳፈርና አዲሱን የቅኝ ግዛት ቀንበር ለመጫን የሚደረግ ሤራ ነው፤ ለጥቁር ሕዝብ ክብርና ልዕልና ስትሉ፣ በፓን አፍሪካ መንፈስ ሁላችሁም ጥቁር ሕዝቦች ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቆሙ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ ማለታቸው ይታወሳል።