ቀጥታ፡

በ2010 በጀት ዓመት በዲፕሎማሲው መስክ ስኬታማ ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ

አዲስ አበባ ነሃሴ 16/2010 በኢትዮጵያ በ2010 በጀት ዓመት በዲፕሎማሲው መስክ ስኬታማ ውጤት መመዝገቡን የዉጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ፡፡ ሚኒስቴሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ባከናወነቻቸው የውጭ ግንኙነት ተግባራት፣ በ2011 እቅድ እና በወቅታዊ የአገሪቱ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጉዳዮች ዙሪያ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ የተለያዩ አገራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ፈተናዎችን ተቋቁማ ከመቼውም ጊዜ የላቀ ውጤታማ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ አፈፃፀም አስመዝግባለች። ከስኬቶቹ መካከል ግንባር ቀደም የሚባለው በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የነበረው ለአመታት የቆየ አለመግባባት በሰላም መፈታቱ መሆኑን ቃል አቀባዩ ገልፀዋል። ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ተስፋ ቆርጦ የተወው የኢትዮ-ኤርትራ ችግር በሁለቱ አገሮች መሪዎች መልካም አሳቢነት ተፈትቶ  ሰላማዊ ግንኙነት እውን የሆነበት ዓመት መሆኑን አስረድተዋል። የኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ሰላም መምጣት ከሁለቱ አገሮች በላይ በአፍሪካ አካባቢያዊ ፖለቲካ ላይ የሚኖረው አንድምታ የጎላ መሆኑንም ቃል አቀባዩ ጨምረው ገልጸዋል። ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባለፈ የጋራ መሰረተ ልማት ፈንድ ለማቋቋም የሚያስችል ስምምነት ማድረጋቸውም የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ስኬት እንደነበረ ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳንን እና ሶማሊያን ጨምሮ በአጠቃላይ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ሰላም ለማምጣት በተደረጉት የተለያዩ ጥረቶች የኢትዮጵያ ሚና ጉልህ ነበር። ኢትዮጵያ በምትከተለው ነፃነት፣ ገለልተኛነትና ተገማችነትን መርሁ ያደረገ የዲፕሎማሲ አካሄድ በሁሉም ዘርፎችና አቅጣጫዎች ስኬት አስመዝግባለች ነው ያሉት ቃል አቀባዩ። የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ለኢትዮጵያ ካላቸው ቅርበት፣ ታሪካዊ ግንኙነትና ትልቅ አቅም አንጻር አገሪቱ ከአካባቢው አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ጥረት የተደረገው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት መሆኑን አስረድተዋል። ኢትዮጵያ ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የምታራምድ አገር በመሆኗ በአፍሪካ ህብረት፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ)፣ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የመሪነት ሚናዋ የጎላ እንደነበር ቃል አቀባዩ ጨምረው ጠቁመዋል። በኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ ዘርፍም 4 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ያስመዘገቡና በዓለም ላይ ግዙፍ የሚባሉ 156 የውጭ ኩባንያዎች  በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ መደረጉን ገልጸዋል። "መንግስት ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን ጋር የነበረውን የጥላቻ ግንብ በመናድ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በያገባኛል ስሜት እንዲንቀሳቀሱ ስምምነት ላይ ደርሷል"  ያሉት አቶ መለስ ዳያስፖራው በአገሩ ጉዳይ ጠንካራ ተሳታፊ ሊሆን የሚችልበት ምቹ ድባብ መፈጠሩን ተናግረዋል። የተለያዩ አገሮች ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ያላቸው ፍላጎት መጨመር፣ ዳያስፖራው በአገሩ ጉዳይ ላይ ለመሳተፍ ቁርጠኛ መሆን ለቀጣይ የዲፕሎማሲ ስራዎች መልካም አጋጣሚ እንደሆነ አቶ መለስ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ከዚህ በላይ እንዲጎለብት፤ የአገር ውስጥ ሰላም መጠናከር እንዳለበት የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፤ ለዚህም አገሪቱ ያላትን ምቹ ሁኔታ ሁሉ በአግባቡ መጠቀም የሚያስፈልግ መሆኑን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚኖረውና ኢትዮጵያም በንቃት የምትሳተፍበት የቻይና አፍሪካ ፎረም በቅርቡ እንደሚካሄድም ገልጸዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም