በአዲስ አበባ የአትሌቲክስ ማዘውተሪያ ስፍራዎች መጥፋት ዘርፉ እንዳያድግ እንቅፋት ሆኗል - አትሌቶች - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የአትሌቲክስ ማዘውተሪያ ስፍራዎች መጥፋት ዘርፉ እንዳያድግ እንቅፋት ሆኗል - አትሌቶች
አዲስ አበባ ነሀሴ 16/2010 በአዲስ አበባ ከተማ ለአትሌቲክስ ስፖርት ማዘውተሪያ የሚሆኑ ምቹ ሥፍራዎች ከጊዜ ወደጊዜ በመመናመናቸው በስፖርቱ ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እየፈጠረ መሆኑን ታዋቂ አትሌቶች ገለፁ። የከተማ አስተዳደሩ ለአትሌቲክስ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚሆኑ ስፍራዎችን እንዲያዘጋጅም አትሌቶቹ ጠይቀዋል። የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ችግር መኖሩን የሚገልፀው የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት ከአትሌቶቹና ከሚመለከተው አካል ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ እንደሆነ አመልክቷል። የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አትሌት ስለሺ ስህን እንደሚለው በመዲናዋ ለአትሌቶች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ የሚሆን ስፍራ መጥፋት በአትሌቲክስ ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። አትሌቶች የሩጫ ልምምድ የሚያካሄዱባቸው ስፍራዎች በአሁኑ ወቅት ቆሻሻ መጣያ እና ልዩ ልዩ ግንባታ የሚከናወኑባቸው መሆናቸውን አትሌት ስለሺ ገልጿል። አዲስ አበባ ሩጫን ጨምሮ የተለያዩ አትሌቲክስ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ ከተማ ብትሆንም በአሁኑ ወቅት ታዳጊዎች፣ ወጣቶችና ጎልማሶች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የመችሉበት ምቹ ስፍራ መመናመኑንም ጠቁሟል። ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመለወጥ አትሌቶችም የመፍትሔ አካል እንደሚሆኑ ያረጋገጠው አትሌት ስለሺ ችግሩን ለመፍታት በሚከናወኑ ማናቸውም ተግባራት የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል። አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በበኩሉ በአሁኑ ወቅት አትሌቶች ለስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የሚጠቀሙባቸው ጃንሜዳና አራራት አካባቢ ያሉት ስፍራዎች የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሆነዋል። በተለምዶ አራራት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውና በአትሌት ቀነኒሳ ስም የተሰየመው ፓርክ ለአትሌቶች መለማመጃ ቦታ እንዲሆን ተገቢው የልማት ሥራ እንዲከናወንለትም አትሌት ቀነኒሳ ጠይቋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ እንደሚለው፤ በመዲናዋ ለአትሌቲክስ ስፖርት ማዘውተሪያ የሚሆን ቦታ እጥረት አለ። ታዳጊዎች አትሌቲክስ ስፖርትን እያዩ እንዲያድጉ የሚችሉበት ዕድል ማጣታቸውን ገልጿል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የአትሌቲክስ ስፖርት ማዘውተሪያን በተመለከተ የሚነሳው ቅሬታ ትክክል መሆኑን አረጋግጠዋል። ኢትዮጵያ በዓለም የምትታወቅበት የአትሌቲክስ ስፖርት ውጤታማ እንዲሆን ለችግሩ መፍትሔ ለማበጀት የከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።