ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ነጻነት እስኪረጋገጥ ወደ ኋላ አንልም፤ የምንፈልገው እኛ ሞተን የምትቆም ኢትዮጵያን ማየት ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

ህዳር 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) “የኢትዮጵያ ነጻነት እስኪረጋገጥ ወደ ኋላ አንልም የምንፈልገው እኛ ሞተን የምትቆም ኢትዮጵያን ማየት ነው” ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።

የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የግንባር አውዶችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።በመግለጫቸው “የሠራዊቱ ሞራል እጅግ ደስ ይላል ጦርነቱ በከፍተኛ ድል ነው እየተከናወነ ያለው” ብለዋል።

“የኢትዮጵያ ነጻነት እስኪረጋገጥ ወደ ኋላ አንልም የምንፈልገው እኛ ሞተን የምትቆም ኢትዮጵያን ማየት ነው” ሲሉም አስታውቀዋል።

የምንፈልገው ኢትዮጵያዊ መሆን ወይንም ኢትዮጵያ መሆንን ነው በማለት ገልጸው፤ “ይህንን ደግሞ በድል እናሳካዋለን” ሲሉ አረጋግጠዋል።

ህዝባችን ከጎናችን ነው በማለት የህዝቡን ከፍተኛ ድጋፍ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በውጭ ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ምሁራን ባላቸው አቅም የኢትዮጵያን ድምጽ እያሰሙ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በአንድ ቀን ውጊያ ትልቅ ድል መመዝገቡን ገልጸው፤ “ከዚህ በኋላ ትልልቅ ድሎች እንደሚጠብቁ እና ጠላት ከኛ ጋር ሊፎካከር የሚያስችል ቁመና የለውም” ብለዋል።

“እናሸንፋለን ነጻ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን እናሸጋግራለን፣ ይህን ለማድረግ ነው እዚህ ያለነው ውጤቱ የሚያኮራ ነው” ሲሉም አስታውቀዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣ _

ወደ ግንባር ዝመት፣_

መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም