ቀጥታ፡

አንዳንድ የምዕራብ አገራት አሸባሪውን የህወሐት ቡድን በግልጽ እየደገፉ ነው

ኅዳር 17/2014 (ኢዜአ) በቅርቡ የወጣው ድብቅ ስብሰባ አንዳንድ የምዕራብ አገራት አሸባሪውን ህወሓትን እየደገፉ መሆኑን ማሳያ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ አሜሪካዊያን የዜጎች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ ተናገሩ።
ከትናንት በስትያ ለአሸባሪው ህወሓት የወገኑ አንዳንድ ኢትዮጵያዊያን እና የምዕራብ አገራት የፖለቲካ ሰዎች ቡድኑን ለመደገፍ የተሳተፉበት ድብቅ ስብሰባ ይፋ ወጥቷል።

በዚህ ድብቅ ስብሰባ አምባሳደር ብረሃነ ገብረክርስቶስ፣ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ፣ ዶክተር እሌኒ ገብረ መድህን፣ ፕሮፌሰር ጥላሁን በየነ፣ አምባሳደር በቀለ ገለታ እና ዶክተር ታደሰ ውሂብ ተሳትፈዋል።

በሌላ በኩል በሶማሊያ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ፣ የቀድሞ የአሜሪካ የመከላከያ የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ ቪኪ ኹደልስተን፣ የአውሮፓና የእንግሊዝ ዲፕሎማቶች በስብሰባው ታድመዋል።

የስብሰባው ዋነኛ ዓላማ በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በማውረድ የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም ያለመ ሲሆን ቀጣይ የኢኮኖሚ አቅጣጫም የተመላከተበት ውይይት ነበር።

ኢዜአ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ አሜሪካዊያን የዜጎች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ፤ ስብሰባው ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መግባታቸውን ያሳያል ብለዋል።

በተለይም ደግሞ አንዳንድ የምዕራባዊያን አገራት በሕዝብ ድምጽ ወደ ሥልጣን የመጣውን መንግሥት ለመገልበጥ ለሚሰራው ለአሸባሪው የህወሓት ቡድን እያደረጉ ያለውን ድጋፍ በግልጽ ያሳያል ነው ያሉት።

እነዚሀ አገራት በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ሥልጣን የመጣውን መንግሥት ለማውረድ የሚሸረበው ሴራ አካል መሆናቸው በ6ኛው አገራዊ ምርጫ የተሳተፈውን 40 ሚሊዮን ሕዝብ ድምጽ መናቅ ነው ብለዋል።  

ይህም ሕገወጥና ፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አንስተው ምዕራባዊያኑ ይህንን የሚያደርጉት የራሳቸውን ፍላጎት የሚያስጠብቅላቸው መንግሥት ለመመሥረት አስበው መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ዶክተር እሌኒ ገብረመድህን የዓለም አቀፍ ተቋም ሠራተኛ ሆነው አቋም በመያዝ በዚህ ድብቅ ሰብሰባ በመሳተፋቸው ከተቋሙ አሰራር ውጪ መንቀሳቀሳቸውን ነው የገለጹት።

ዲያቆን ዮሴፍ ይህንን የሚመለከተው አካል ጉዳዩን ሊያጤነውና ምላሽ ሊሰጥበት እንደሚገባ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።  

እነዚህ አገራት ከዚህ አይነቱ ተግባራት ራሳቸውን ማራቅ እንዳለባቸው አስገንዝበው አሜሪካዊያን የዜጎች ምክር ቤትም ይህ እንዲሆን ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም ደግሞ ይህንን ሕገ-ወጥ ስብሰባ በተመለከተ የሚመለከታቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጉዳዩን እንዲመለከቱትና መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች እንዲያስተካክሉ እንሰራለን ብለዋል።

ሕዝቡ በማኅበራዊ ሚዲያ በተለይም በትዊተር የኢትዮጵያን እውነታ በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ በማጋራት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንዲከበር የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።  

ይህም በተለይም በዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚሰራጩ የሃሰት መረጃዎችን ጭምር ለመከላከል እንደሚጠቅም ዲያቆን ዮሴፍ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም