በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአይበገሬነት ታሪካችንና የትውልዱን ጀግንነት ታድሷል-ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአይበገሬነት ታሪካችንና የትውልዱን ጀግንነት ታድሷል-ፓርቲዎች
ሐዋሳ ኅዳር 17/2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ግንባር መዝመታቸው የኢትዮጵያውያን የአይበገሬነት ታሪክና የትውልዱን ጀግንነት እንደሚያድሰው የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።
ፓርቲዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመታቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያቀረቡት አገራዊ ጥሪ የወገንን አቅም የገነባ ፤ ጠላትን ደግሞ ያስደነገጠ ብለውታል።
በደቡብና በሲዳማ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች አመራሮች ለኢዜአ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትውልዱ ከቀደምት አባቶችና እናቶች የወረሰውን ታሪክ በዘመኑ እንዲደግም አነሳስተውታል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ(ኢዜማ) የሲዳማ ክልል ተወካይ አቶ እንግዳወርቅ አሰፋ እንዳስታወቁት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ውሳኔ ጊዜውን የዋጀና የዜጎችን አቅምና ሞራል የሚገነባ ነው።
በተለይም ጠላትን ለሚፋለሙት የጸጥታ ኃይሎች ተጨማሪ አቅምና ጉልበት እንደሚሆን አመልክተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ውሳኔ ለወገን አቅምና ሃይል የሰጠ አሸባሪውን ህወሓት የሚጋልቡትን ታሪካዊ ጠላቶች ደግሞ ያስደነገጠ መሆኑን ተናግረዋል።
''አሁን ላይ ሁሉም ዜጋ በመሪው ስለኮራ በወኔ ነው የሚንቀሳቀሰው'' ያሉት አቶ እንግዳወርቅ ''ለእናት አገር መሞት ክብር ነውና ሙሉ ዝግጅት አድርጌያለሁ'' ሲሉ ገልጸዋል።
"በኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት የለውጥ መንግስት ከመጣ ወዲህ ሁሉም ፓርቲዎች ካለምንም ልዩነት አገርን በማስቀደም እየሰራን ነው" ያሉት ደግሞ የአዲስ ትውልድ ፓርቲ የሲዳማ ተወካይ አቶ አበራ ሙዴ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተከትለው በመዝመት ጠላትን ድባቅ በመምታት አኩሪ ታሪክ እንደሚመዘገብ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ)የደቡብና ሲዳማ ቀጠና አስተባባሪ አቶ አቻ ለገሰ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአገርን ህልውና ለማስከበር መዝመታቸው ታሪክ እንደ ሚዘክራቸው ገልጸዋል።
''ኢትዮጵያውያን ቆራጥ መሪ በማግኘታችን መኩራት አለብን'' ያሉት አስተባባሪው እሳቸውም የመሪያቸውን ፈለግ ተከትለው ለመዝመት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን በመቆም ለሥልጣን ብለው አገር ለማፍረስ ከጠላት ጋር የሚደራደሩ ባንዳዎችን በማስወገድ ማንነታችንን እንደሚያስከብሩና ታሪካችንን እንደሚያድሱ ገልጸዋል።