በኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች ዓለምን በጥበብ ማቀፍና መልእክቶቻችንን ማስተላለፍ እንችላለን

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች አብሮነትና አንድነታችንን አጠናክረን ዓለምንም በጥበብ ማቀፍና መልእክቶቻችንን ማስተላለፍ እንችላለን ሲል የኢትዮጵያን የጃዝ ሙዚቃ ንጉስ ሙላቱ አስታጥቄ ተናገረ።

የኢትዮጵያን የሙዚቃ ጥበብ እንዴት አድርገን የፍቅር፣ አብሮነት፣ የሰላም መገለጫዎች ማድረግ እንችላለን? በአፍሪካ ብሎም በዓለም ላይ ማንነታችንን የምናስተዋውቅበት፤ መልእክቶቻችንን የምናስተላልፍበት ማድረግ እንችላለን?

በዚህ ዙሪያ ኢዜአ የኢትዮጵያን የጃዝ ሙዚቃ ንጉስ የክብር ዶክተር ሙላቱ አስታጥቄን እንዲሁም ተወዳጁን አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ አነጋግሯል።

ታላቁ የጃዝ ሙዚቃ ንጉስ ሙላቱ አስታጥቄ፤ ኢትዮ ጃዝ የተባለውን የሙዚቃ ስልት በመፍጠር ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ አስተዋውቋል።

አርቲስቱ ለዓለም የሙዚቃ እድገት ስላደረገው የላቀ አስተዋፅኦም በቦስተን የሚገኘው የበርክሊ የሙዚቃ ኮሌጅ ሙላቱን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቶታል።

የክብር ዶክተር ሙላቱ፤ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች አብሮነትና አንድነታችንን አጠናክረን ዓለምን በጥበብ ማቀፍና መልእክቶቻችንንም ማስተላለፍ እንችላለን ይላል።

የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች የአፍሪካ ብሎም የዓለም ውድ ሃብቶች በመሆናቸው ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አንድነትንና አብሮነትን የምንሰብክባቸው መድረኮች ማድረግ እንችላለን ብሏል።

የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች በተለያዩ መድረኮች ኢትዮጵያ ለአለም ያበረከተችውን ሁሉ ለማሳየት እድሉ ስለሚኖራቸው ሊጠቀሙበት ይገባልም ነው ያለው።

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ላለፉት 30 አመታት የሰራውና አሁንም እያገለገለ የሚገኘው ድምጻዊ ዘለቀ ገሰሰ፤ ምእራባውያን አገራት ሊከፋፍሉን በጥረት ላይ በመሆናቸው ሁላችንም ልንመክታቸው እንዘጋጅ ይላል።

በዚህ ጊዜ በተለይ ጥበብ ብዙ መልእክት የምናስተላልፍበት በመሆኑ ያለንን ቱባ ባህል አውጥተን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ብሏል።

የኢትዮጵያ አርቲስቶች አሁን ላይ አፍሪካን ማእከል ያደረጉ ሙዚቃዎች ላይ ትኩረት አድርገን ልንሰራ ይገባልም ነው ያለው አርቲስት ዘለቀ።

ለአለም በስፋት ተደራሽ በሚሆኑ ቋንቋዎች ላይ አተኩረን አገራችንን ማስተዋወቅና መልእክቶችን ማስተላለፍ ይጠበቅብናል ብሏል።

አርቲስቶቹ በመልእክታቸው ሙዚቃችን በዓለም ላይ የሚያስተጋባ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

አብሮነታችን የአገር መከታና ካባ መሆን አለበት ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም