የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ሁሉም በጋራ መቆም አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ሁሉም በጋራ መቆም አለበት
ኀዳር 16/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ሁሉም በጋራ መቆም እንዳለበት የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ገለጹ።
የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ቢሮ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የሃይማኖት አባቶች፤ የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ሁሉም በጋራ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።
እምነትም ሃይማኖትም አገር ስትኖር በመሆኑ ሁላችንም ለኢትዮጵያ ሰላም፣ አንድነትና ሉአላዊነት በጋራ እንቁም ሲሉ ጠይቀዋል።
የሃይማኖት ተቋማት የአገሪቱንና የህዝቡን ሰላም ለማስፈን በጾም ጸሎት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው የአገርን ዳር ድንበር ማሰጠበቅ የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን ጠቅሰዋል።
መለዕክ ሰላም በክሩ ወልደሚካሄል ና ቄስ ከበደ አባው እንዲሁም ሃጂ ሃይሉ አብዶ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘምቶ አገሩን በመጠበቅ፣ ሰራዊቱን በመደገፍ እንዲሁም የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ በመጠበቅ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለበት ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ከየአቅጣጫው የተከፈተብንን ጦርነት በአንድነት እንቀለብሰዋለን ኢትዮጵያን ሊያፈርሳት የሚችል ሃይል የለም ብለዋል።
የከተማው ነዋሪዎች በቅንጅት አካባቢያቸውን በመጠበቅ የአሸባሪዎችን ሴራ ማክሸፍ አለባቸውም ሲሉም ጠቁመዋል።
አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ "ሲኦል እገባለው" ማለቱን አስታውሰው "ሲኦል ይገባል አገራችንን ግን አያፈርሳትም" ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶች የአሸባሪው አገር ለማፍረስ እየሰራ ያለውን ሴራ ለተከታዮቻቸው ማስገንዘብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ቀደምት አያቶች ኢትዮጵያን ከነክብሯ አስረክበውናል እኛም ልናስከብራት ዝግጁ ነን ብለዋል።
አሸባሪው ከውስጥና ከውጭ ሃይሎች ጋር ግንባር ፈጥሮ የኢትዮጵያን ህልውና ለማፍረስ ጦርነት ቢከፍትም በቆራጥ ልጆቿ ትግል እየከሸፈ መሆኑን ገልጸዋል።