ኢሶዴፓ እና እናት ፓርቲ አመራሮች በግንባር በመሰለፍ ጭምር ለህልውና ዘመቻው ስኬት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢሶዴፓ እና እናት ፓርቲ አመራሮች በግንባር በመሰለፍ ጭምር ለህልውና ዘመቻው ስኬት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ገለጹ
ህዳር 16/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሶሻል-ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) እና እናት ፓርቲ አመራሮች በግንባር በመሰለፍ ጭምር ለህልውና ዘመቻው ስኬት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ገለጹ፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በህልውና ዘመቻው ተሳትፎ በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላቀረቡት ጥሪ ምላሽ እንዲሰጥም ነው ፓርቲዎቹ ጥሪ ያቀረቡት፡፡
ፓርቲዎቹ ለኢዜአ በላኩት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ አሸባሪው ህወሃት በትዕቢትና ትምክህት ተሞልቶ "ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ" በሚል ቅዥት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ግፍ እየፈጸመ ይገኛል፡፡
በመሆኑም የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ግንባር ዘምተው የህልውና ዘመቻውን ለመምራት መንቀሳቀሳቸው ተገቢና ወቅቱን የጠበቀ ውሳኔ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ለህልውና ዘመቻው ስኬት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብሎ ፓርቲያቸው እንደሚያምንም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አንጻር የፓርቲያቸው አባላትና ደጋፊዎች ለዚሁ ዘመቻ ስኬት ተሳትፎ እንዲያደርጉም ነው መልዕክት ያስተላለፉት፡፡
ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ህልውና ማስጠበቅ የሚችሉት ታግለው በማሸነፍ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ በህልውና ዘመቻው ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የኢሶዴፓ እና እናት ፓርቲ አመራሮች በግንባር በመሰለፍ ጭምር ለህልውና ዘመቻው ስኬት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ በላኩት መግለጫ አረጋግጠዋል፡፡
በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን የውጭ ጫና እና የሀሰተኛ መረጃ ዘመቻ አጥብቀው እንደሚቃወሙም አስታውቀዋል፡፡