በካሊፎርኒያ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት በ5 ሠዓታት ያሰባሰቡትን 11 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ አበረከቱ - ኢዜአ አማርኛ
በካሊፎርኒያ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት በ5 ሠዓታት ያሰባሰቡትን 11 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ አበረከቱ
ህዳር 16/2014 (ኢዜአ) አሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት በ5 ሠዓታት ውስጥ ያሰባሰቡትን 11 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ለአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስረክበዋል።
በተመሳሳይ በስዊዘርላንድ ከሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት 1 ሚሊዮን 700 ሺህ ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ መረከቡን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በካሊፎርኒያ ቤይ አካባቢ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ድጋፍ አስተባባሪ አቶ ምኒልክ አንዳርጌ የተሰበሰበውን 10 ሚሊዮን 810 ሺህ 919 ብር ለአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስረክበዋል።
ዳያስፖራው አገሩንና ወገኑን ለመርዳት በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንና፤ ገንዘቡም አሸባሪው ህወሓትና ግብረ አበሮቹ በከፈቱት ጦርነት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች እንደሚውል ገልጸዋል።
በውጭ አገራት የሚኖሩ በሃሳብ ግን አገራቸው ውስጥ ያሉ፤ ስለ አገራቸውና ወገናቸው የሚቆረቆሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን ገልጸዋል።
አገር የገጠማትን ፈተና በአንድነት መንፈስ መወጣት እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአደጋ ስጋት አመራር ምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ ያሲን በበኩላቸው ጦርነቱ የእጅ አዙር መልክ ስላለው በተለይ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ከማቅረብ አኳያ ከተራድኦ ድርጅቶችና ከአንዳንድ መንግስታት የሚጠበቀውን ያህል ድጋፍ እየተገኘ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የገጠማትን የእጅ አዙር ጦርነት በመረዳት ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውንም ገልጸዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው እያደረጉት ላለው ድጋፍ አመስግነው፤ ድጋፉ ኮሚሽኑ በዘረጋው አሰራር ለተፈናቀሉ ወገኖች እንደሚደርስ ተናግረዋል።
የተሰባሰበው ድጋፍ በተለይም ለተፈናቃይ ሴቶች፣ ሕፃናትና አቅመ ደካሞች ቅድሚያ የሚሰጥበትን መንገድ በመፍጠር ግልፅነት ባለው መልኩ ተደራሽ ይሆናል ሲሉም አክለዋል።
በተመሳሳይ ዛሬ በስዊዘር ላንድ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ከ1 ሚሊዮን 700 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የአይነት ድጋፍ ለኮሚሽኑ አስረክበዋል።
የተደረገው የአይነት ድጋፍ የስንዴ ዱቄት፣ የምግብ ዘይትና አልሚ ምግብ ሲሆን ይህም ለተፈናቃዮች የሚሰራጭ ይሆናል።
በተያዘው ሳምንት ብቻ ከኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ሰራተኞች 700 ሺህ፣ ከኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ሠራተኞች 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን፣ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሰርጀሪ ዲፓርትመንት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በጥቅሉ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ መገኘቱን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ኤምባሲ 74 ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆነ ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል።