ቀጥታ፡

በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ለማስቆም የህልውና ዘመቻውን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል-ሚኒስቴሩ

ባህርዳር ህዳር 16/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚያደርሰውን መከራና ስቃይ ለማስቆም የህልውና ዘመቻና ትግሉን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

አሸባሪ ቡድኑ የአማራ ክልል በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ብቻ ከ7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በምግብና መድሃኒት እጦት ለከፋ ችግር መጋለጣቸው ተመላክቷል።

የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም በባህር ዳር ከተማ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ  እንደገለጹት አሸባሪ ቡድኑ በንጹሃን ዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለው የጭካኔ ድርጊት በዓለም ላይ አልታየም።

ንጹሃንን በመግደል፣ ሴቶችን በቡድን በመድፈር፣ የህዝብና የመንግስት ሃብትን በመዝረፍ፣ በማውደምና መሰረተ ልማትን በማፈራረስ እስካሁን በኢትዮጵያ ታሪክ ተሰምቶ የማያቅ ግፍ ፈጽሟል።

"ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ወራሪ ቡድኑ በደረሰባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶችን በግድ ወደ ጦር ግንባር በማሰለፍ የጥይት ማብረጃ በማድረግ የመጨረሻውን የግፍ ጥጉን እያሳየ ይገኛል" ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት ከዚህ በላይ እድል ካገኘ በንጹሃን ላይ ተጨማሪ በደል ከማድረስ ባለፈ አገር ከማፍረስ ወደ ኋላ እንደማይል በተግባር ማሳየቱን ነው የገለጹት።

ቡድኑ የሚፈጽመውን ግፍና በደል ለማስቆም ዋናው መፍትሄ ወረራውን ለመቀልበስ የተጀመረውን የህልውና ዘመቻና ትግል አጠናክሮ ማስቀጠል መሆኑን አመልክተዋል።

ዜጎችን ነጻ ለማውጣትና ሀገርን ከመፍረስ ለመታደግ በሚደረገው ትግል ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

"በአማራ ክልል በአጠቃላይ ከተፈናቀለው ህዝብ አብዛኞቹ ሴቶች፣ ህጻናት፣ አረጋውያን፣ የአካል ጉዳት ያለባቸውና ሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው" ያሉት ደግሞ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ናቸው።

የህብረተሰብ ክፍሎቹን ለመደገፍ በዕድሜ፣ በጾታ፣ በጉዳት መጠንናና በሌሎች መስፈርቶች ተጨባጭና ዝርዝር መረጃ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

"በወረራው የተፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ ወደ ማህበራዊ ቀውስ ተሸጋግሮ ዘላቂ የሀገር ችግር እንዳይሆን ረጅ ድርጅቶችም የሚችሉትን ያህል እንዲደግፉ መጣር ያስፈልጋል" ብለዋል።   

ለከተማ ሴፍትኔት ፕሮግራም የተመደበን 700 ሚሊዮን ብር ለተፈናቃዮች ድጋፍ ለማዋል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን በበኩላቸው "የውጭ ረጅ ድርጅቶች ወደ ተግባር አለመግባት በጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎችን በመደገፍ በኩል መሰረታዊ ለውጥ እንዳይመጣ አድርጓል" ብለዋል።

"ከተባበሩት መንግስታት ድርጅቶችና ከአሜሪካ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ጋር በችግሩ ስፋትና ጥልቀት ላይ በመምከር በተደጋጋሚ ለማስረዳት ቢሞከርም በሌሎች አካባቢዎች እንዳደረጉት ወደ  አማራ ክልል ገብተው ሊደግፉ አልቻሉም" ሲሉ አመልክተዋል።

የዜጎች መፈናቀል ችግር ሲከሰት ጀምሮ ፈጥኖ በመድረስ የተፈናቃዮችን ህይወት በመታደግ ረገድ የአካባቢ ማህበረሰብና ዩኒቨርሲቲዎች ትልቅ አስተዋጾ እንዳላቸው ተናግረዋል።

በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ በበጎ አድራጎት ሥራ የተሰማሩ አካላትም ሃብት በማሰባሰብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመው፣ በፌደራል ደረጃም ድጋፉን ፈጥኖ የማጓጓዝና ለተረጂዎች የማድረስ አቅምን መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

"በክልሉ የደረሰውን ችግር ለመፍታት በወረራ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ሁኔታ፣ የተፈናቃዮችና መልሶ መቋቋምን ያገናዘበ ሥራ መስራት ያስፈልጋል" ያሉት ደግሞ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ናቸው።

"ከዓለም አቀፍ ረጅ ድርጅቶች ጋር በተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ ችግሩን ለማሳየት ቢሞከርም ፈጣን ምላሽ እየተሰጠ አይደለም" ብለዋል።

ኮሚሽነሩ እንዳሉት የረጅ ድርጅቶቹ  ፍላጎት መሰረት የሚያደርገው የገንዘብ ምንጭ የሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መንግስታትን ፈቃድ ነው።

"በመሆኑም ከዚህ በኋላ ገንዘብ ያለው ገብቶ እንዲሰራ ፣የሌለው እንዲወጣ ውሳኔ ማሳለፍ ያስፈልጋል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም