ቀጥታ፡

የመረጃ ነፃነት አዋጅን የማሻሻል እንቅስቃሴ ተጀምሯል

ህዳር 16/2014 /ኢዜአ/ የመረጃ ነፃነት አዋጁን ለማሻሻል እንቅስቃሴ መጀመሩን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ገለጸ።
ተቋሙ የመረጃ ነጻነት ቀን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።   

በአገሪቷ የመረጃ ነጻነት መብት እየተሻሻለ ቢመጣም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሆኗል ማለት እንደማይቻል የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ ዘውዱ ወንድም ተናግረዋል።

ለመረጃ ነፃነት መብት መሻሻል ምክንያት ሲጠቅሱም ጋዜጠኞች በአንጻራዊነት የሚገደቡበት ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱን አንስተዋል።  

መረጃ የማግኘት መብት ቢኖርም ገደብ መኖሩን የገለጹት ዳይሬክተሩ የመረጃ ነጻነትና የሕግ የበላይነት ተጣጥመው አለመተግበራቸው ከችግሮቹ መካከል ጠቅሰዋል።

ዋነኛ የመረጃ ምንጭ የሆኑት አስፈጻሚ አካላት በሚፈለገው ደረጃ መረጃ እየሰጡ አለመሆኑን ጠቁመው ይህም ኅብረተሰቡን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ለሚለቀቁ  አሉባልታዎች ተጋላጭ አድርጎታል ብለዋል።

በአንድ አገር የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ቀውሶች ሲከሰቱ ዜጎች ግልጽ መረጃ ማግኘት እንዳለባቸው ቢቀመጥም በአግባቡ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ለማለት እንደሚያስቸግር ተናግረዋል።

መገናኛ ብዙሃንም መረጃ ሲያጡ 'ተከለከልን' ከማለት በቀር በተግባር መታገል ላይ ክፍተት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ዘውዱ ገለጻ እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለማቃለል የመረጃ ነጻነት አዋጁን ለማሻሻል እንቅስቃሴ ተጀምሯል።     

በሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የመረጃ ነጻነት ዳይሬክተር አቶ ማናዬ ዓለሙ በበኩላቸው የአንድ ተቋም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ስለ ተቋሙ በጎ ጎን ብቻ የሚያነሳ መሆኑ ሌላው የመረጃ ነፃነት ችግር ነው ይላሉ።

ሕዝብ ስለ አንድ ተቋም ሙሉ መረጃ ማግኘት እንደሚገባው የገለጹት ዳይሬክተሩ የአዋጁ መሻሻል እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን ይፈታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

የአንድ ተቋም ኃላፊ መረጃ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት፤ ካልሰጠም ተጠያቂ የሚሆንበት ሁኔታ ለመፍጠር የአዋጁ መሻሻል እገዛ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

አቶ ማናዬ እንደሚሉት ተቋሙ መረጃን ከማግኘት ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት አሰራር እየዘረጋ ነው።

በተለይ መገናኛ ብዙሃን ለሚያቀርቡት ቅሬታ ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም በመገናኛ ብዙሃኑ በኩል ተከታትሎ የመፍትሄ አካል መሆን ላይ ድክመት አለ ብለዋል።   

6ኛው ዓለም አቀፍ የመረጃ ነፃነት ቀን በኢትዮጵያ ለ4ኛ ጊዜ ሕዳር 18 ቀን 2014 አዳማ ላይ እንደሚከበር ተገልጿል።

በመርሃ ግብሩ በመረጃ ነጻነት ይዘትና ጽንሰ ሀሳቦች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የፓናል ውይይቶች ይከወናሉ፤ የተሻለ ተሞክሮ ያላቸው ተቋማትም ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ይደረጋል።

በቀውስ ወቅት አገሪቷ በመረጃ አሰጣጥ ዙሪያ ምን ደረጃ ላይ እንዳለች የሚዳስስ ጽሁፍ እንደሚቀርብና ውይይትም እንደሚካሄድበት የወጣው መርሃ ግብር ያስረዳል።

በኢትዮጵያ የዲጂታል ሚዲያ ጠቀሜታና ተያያዥ ችግሮች ላይም ገለጻ እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል።

የመረጃ ነጻነት ቀን መከበር የጀመረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ74ኛ ጠቅላላ ጉባኤው ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው።

በዚሁ መሰረት ቀኑ እንደ አውሮጳዊያኑ ዘመን አቆጣጠር በየዓመቱ መስከረም 28 ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም