በአዲሱ አሰራር መሰረት የተሽከርካሪ ምትክ ሰሌዳ አገልግሎት የሚሰጠው አገልግሎት ጠያቂው ሠሌዳ በወሰደበት ክልል ወይም ክፍለ ከተማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ አሰራር መሰረት የተሽከርካሪ ምትክ ሰሌዳ አገልግሎት የሚሰጠው አገልግሎት ጠያቂው ሠሌዳ በወሰደበት ክልል ወይም ክፍለ ከተማ ነው
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 16/2014(ኢዜአ) በአዲሱ አሰራር መሰረት የተሽከርካሪ ምትክ ሰሌዳ አገልግሎት የሚሰጠው አገልግሎት ጠያቂው ሠሌዳ በወሰደበት ክልል ወይም ክፍለ ከተማ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ የተሸከርካሪ ሰሌዳ እጥረት አለመኖሩንም አስታውቋል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር የአስፈፃሚ አካላትን አደረጃጀት ለመወሰን በተዘጋጀው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 መሰረት የስያሜ ለውጥ፣ የስልጣንና ተግባራት ማስተካከያዎች እንዲሁም የተጠሪ ተቋማት ለውጥ ማድረጉን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
ሚንስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ለውጡን ተከትሎ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ይሰጣቸው የነበሩ አገልግሎቶችና የቁጥጥር ስራዎች ወደ ሚኒስቴሩ ተላልፏል።
ሚኒስቴሩ ከባለስልጣኑ በአዋጅ የተላለፉለትን አገልግሎቶች ቀልጣፋና ተደራሽ በሆነ መልኩ ለማከናወን ጥናት ማካሄዱን ገልጸው፤ በዚህም አገልግሎቶቹ በሚኒስቴሩ፣ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በግሉ ዘርፍ እንዲሰጡ መለየቱን ተናግረዋል።
ወደ ግል ዘርፉ ለሚተላለፉ አገልግሎቶች የአሰራር ስርዓት እንደሚዘጋጅላቸው ጠቅሰው፤ ይህ እስኪጠናቀቅ አገልግሎቶቹ በፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት በኩል እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡
በዚህም የተላላፊ ሰሌዳ ምዝገባ እድሳትና ምትክ መስጠት፣ የሰሌዳ ግዢ ማምረት ሰሌዳ ለክልሎች ማሰራጨት ምትክ መስጠት እና ማስወገድ እና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶችን ለጊዜው የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል።
የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የተጠቀሱት ስራዎች የሚያከናውነው ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በሚኖር የአሰራር ስርዓት መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም በአዲሱ አሰራር መሰረት የተሽከርካሪ ምትክ ሰሌዳ አገልግሎት የሚሰጠው አገልግሎት ጠያቂው ሠሌዳ በወሰደበት ክልል ወይም ክፍለ ከተማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሚንስትሯ የሰሌዳ እጥረት እንዳለ ተደርጎ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በሚመለከትም "በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት የሰሌዳ ግብአትም ሆነ የምርት እጥረት የለም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
4 ሺህ 900 ሰሌዳዎች ታትመው መረከብ ለሚፈልጉ ሰዎች ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰሌዳ ማምረት የሚያስችል በቂ ግብዓት መኖሩንም ተናግረዋል፡፡
ወደ አገር ለሚገቡ ተሽከርካሪዎች የሚደረግን የቴክኒክ ምርመራ አገልግሎት ደግሞ በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
እየተከናወነ ባለው የአሰራር ለውጥ ምክንያት አገልግሎቶች አለመቋረጣቸውንም ነው ያነሱት፡፡
የህዝብ ማመላለሻ የስምሪት ፕሮግራም ማፅደቅ፣ በዋና ዋና ኮሪደሮች እና በጎረቤት አገራት የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ማልማት፣ ለተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ ማስገቢያ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት በሚኒስቴሩ በኩል ሳይቋረጡ እየተከናወኑ መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡
ለተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ መስጠትና ማደስ፣ የልዩ ማሽነሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ፈቃድ መስጠትና ማደስ ጨምሮ 10 አገልግሎቶች በክልልና ከተማ አስተዳድር ያሉ መዋቅሮች እንዲተገብሯቸው ተለይተዋል ነው ያሉት።
ከተገለፁት ተግባራት በተጨማሪ የፌዴራል መንጃፍቃድ ለያዙ ተገልጋዮች የእድሳት አገልግሎት በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ይሰጣል ብለዋል።
አገልግሎቶቹን እንዲያከናውኑ ውክልና የተሰጣቸው ተቋማት ሚኒስቴሩ ባወጣቸውና ወደ ፊትም በሚያወጣቸው መመሪያዎች መሰረት አገልግሎት እንደሚሰጡም ተመላክቷል።
የተደረገውን የአሰራር ለውጥ መሰረት የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን፣ የመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት እንዲሁም የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠሪነታቸው ለትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ሆኗል፡፡