የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪና የህዝቡ ምላሽ የቀደመ የኢትዮጵያን ታሪክ መነሻ ያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪና የህዝቡ ምላሽ የቀደመ የኢትዮጵያን ታሪክ መነሻ ያደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ህዳር 16/2014 (ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ጥሪና የህዝቡ ምላሽ የቀደመ የኢትዮጵያን ታሪክ መነሻ ያደረገ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።
በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር ዶክተር ዘመነወርቅ ዮሐንስ፤ ኢትዮጵያን ያስተዳድሩ የነበሩ ቀደምት ነገስታት ጦርነት በሚገጥማቸው ወቅት ለሕዝባቸው ይፋዊ ጥሪ ሲያቀርቡ ህዝቡም ፈጣን ምላሽ በመስጠት ይታወቃል።
አሁንም ኢትዮጵያ የተከፈተባትን የሕልውና ጦርነት ለመመከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን ለሕዝባቸው ጥሪ ያደረጉት የሀገሪቱን የቀደመ ታሪክ በማጤንና የሕዝቡን ጀግንነት በመተማመን ነው ብለዋል።
በዩኒቨርስቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ማርከው መንግስት፣ ቀድሞ የነበሩ የኢትዮጵያ ነገስታት የአገራቸውን ሉአላዊነት ለማስከበር የፈፀሙት አኩሪ ገድል በታሪክ ተሰንዶ ተቀምጧል ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድም የጀግኖች አባቶቹን ገድል በተግባር ለማየት የሚስችለው እድል ተፈጥሮለታል፤ አጋጣሚውን ታሪክ ለመስራት ሊጠቀምበት ይገባል ይላሉ።
ኢትዮጵያዊያን የመሪያቸውን ጥሪ ተቀብለው ለአገራቸው ህልውና ሊዘምቱ ይገባልም ነው ያሉት።
የዩኒቨርሲቲው የፍሬሽማን ኮሌጅ ተባባሪ ዲን ዶክተር ገዛኸኝ ነጋ በበኩላቸው ፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ሕልውና ለማስጠበቅ መዝመታቸው ሁላችንንም አነሳስቶናል ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን በመዝመትም፤ በደጀንነትም በስፋት በመሳተፍ አገራቸውን ሊጠብቁ ይገባል ነው ያሉት።