ፆታዊ ጥቃትን የመከላከልና የማስቆም ተግባር የዘመቻ ብቻ ሳይሆን የሙሉ ጊዜ ስራ ሊሆን ይገባል

120

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 16/2014(ኢዜአ) በሕጻናትና በሴቶች ላይ የሚፈፀመውን ፆታዊ ጥቃት የመከላከልና የማስቆም ተግባር የዘመቻ ብቻ ሳይሆን የሙሉ ጊዜ ስራ ሊሆን ይገባል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቀ ዘውዴ አስገነዘቡ።

ፕሬዚዳንቷ ለ16 ቀናት በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚካሄደውን የጸረ-ፆታዊ ጥቃት ዘመቻ አስጀምረዋል።

አሸባሪው ህወሓት በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በከፈተው ጦርነት በርካታ ሴቶችና ሕፃናት አሰቃቂ ፆታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በሽብር ቡድኑ ወረራ በተፈፀመባቸው አካባቢዎች ፆታዊ ጥቃት ደርሶባቸው በሕክምናና በማገገሚያ ማዕከላት የሚገኙ ህፃናትና ሴቶችና መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በጦርነት ወቅት ሴቶችን የእልህ መወጣጫ የማድረግ አካሄድ ሊቆም ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

ችግሩ አስከፊ በመሆኑ ፆታዊ ጥቃትን የመከላከልና የማስቆሙ ተግባር የአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን የሙሉ ጊዜ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ሴቶች ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙና የሕግ ከለላ እንዲኖራቸው ፖሊሲና ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር እንደሚገባም አመልክተዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው በጦርነቱ በርካታ ሴቶች ሕይወታቸው ተመሰቃቅሎ ያልተገባ ዋጋ እየከፈሉ ነው ብለዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን አባላት በሴት ሕጻናትና አረጋዊያን ላይ ከተራ ትንኮሳ እስከ ሕይወት ማጣት የደረሰ ልብን የሚሰብሩ ተግባራት እንደፈጸመባቸው ተናግረዋል።

እነዚህ የጥቃት ተግባራት ከተፈጸሙባቸው መካከል ማይካድራ፣ ጋሊኮማ፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ እና ሌሎች አካባቢዎችን ጠቅሰዋል።

ወረራ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመውደማቸው ሴቶች ለከፋ ችግር መዳረጋቸውንም አውስተዋል።

ሚኒስትሯ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በየአካባቢው ችግር የደረሰባቸውን ዜጎች ለመታደግ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝም አሳስበዋል።

ችግር ሲከሰት ቀዳሚ ተጎጂዎች ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች በመሆናቸው ሁሉም አካል አስቀድሞ የመከላከል ስራው ላይ ማተኮር አለበትም ብለዋል።

የ16 ቀናት የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ዘመቻው "ሠላም ይስፈን፤ በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚደረግ ፆታዊ ጥቃት ይቁም" በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።

በዘመቻው ጉዳት የደረሰባችውን ዜጎች የመደግፍና ለጥቃት የተጋለጡትንም የመርዳት ስራ ይከናወናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም