ቀጥታ፡

በተሰማራንበት ሙያ ወታደር በመሆን አገራዊ ግዴታችንን እንወጣለን

ህዳር 16/2014(ኢዜአ) በተሰማሩበት የሥራ መስክ ወታደር በመሆን አገራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች ገለፁ፡፡
ወጣቶቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ "ኢትዮጵያ በአሸባሪው ኃይል አትፈርስም" በማለት ወደ ግንባር  መዝመታቸው ለትውልዱ ትልቅ ትምህርት የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወጣት ጌትነት አምሳሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ቀደምት የአገሪቷ መሪዎች የፈፀሙትን ታሪክ እንዲያስታውስ እንዳደረገው ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ አገር እንዳትቀጥል ለማድረግ የተነሳውን አፍራሽ ኃይል ከመንግስት ጎን በመሰለፍ፣ ለሠራዊቱ ደጀን በመሆንና በስራው ሕዝቡን በቅንነት ለማገልገል ቁርጠኝነቱን አረጋግጧል።

የመሪው  ውሳኔ  ሁላችንም ለአንድ ዓላማ በኅብረት እንድንቆም ያደረገ ነው ያለው ደግሞ ወጣት ቴዎድሮስ ዘለቀ ነው።

ወጣት ታምራት ጉልላት በበኩሉ ህወሓት በፈጠረው ችግር ሳቢያ ሕዝቡ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በሌሎች ጉዳዮች መጎዳቱን አንስቷል።

በመሆኑም ይህንን ችግርና ፈተና ለማለፍ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ልናደርግ ይገባል ብሏል።

የአገር ሕልውናን ለማረጋገጥ ወጣቶች በምንችለው አቅም በመዝመት እና የተፈናቀሉትን በመርዳት የራሳችንን ሚና መጫወት ይኖርብናል ያለው ደግሞ ወጣት ካሳው እደግልኝ ነው።

ህወሓት ኢትዮጵያን ለመበታተን የያዘው እኩይ ዓላማ እንዲከሽፍ ከተንቀሳቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም እየደገፈ ይገኛል።

የኢትዮጵያን ነፃነትና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥም የጠቅላይ ሚኒትር ዐቢይ አህመድን ፈለግ በመከተል ታዋቂ ግለሰቦችና የተለያዩ አመራሮች ወደ ግንባር በመሄድ ዘመቻውን ተቀላቅለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም