ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ኢትዮጵያን ለድርድር ከማቀረብ ሞቴን እመርጣለሁ" የሚለውን ቃላቸውን በተግባር እያሳዩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ኢትዮጵያን ለድርድር ከማቀረብ ሞቴን እመርጣለሁ" የሚለውን ቃላቸውን በተግባር እያሳዩ ነው
ህዳር 16/2014(ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ኢትዮጵያን ለድርድር ከማቅረብ ሞቴን እመርጣለሁ" የሚለውን ቃላቸውን በተግባር እያሳዩ መሆኑን አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ተናገሩ።
አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ በረጅም ዓመት ታሪኳ በርካታ ችግሮች በተለይም የውጭ ጥቃቶችን ተቋቁማ ያለፈች አገር ናት ብለዋል።
ምቀኛና ጠላት እንደሚበዛባት ጠቅሰው የዛኑ ያህል ግን ኢትዮጵያ በድል አድራጊነት ሃብታም መሆኗን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አሁን የገጠማት ችግር በውስጥና በውጭ ሃይሎች አገር የማፍረስ ሴራ የሚመራ መሆኑን አንስተው ይህም ኢትዮጵያ በታሪኳ ከገጠሟት ፈተናዎች የተለየ መሆኑን ገልጸዋል።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን "ኢትዮጵያን እኛ ካልገዛናት ትፍረስ" በማለት ለገዛ ሥልጣናቸው በማሰብ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የገቡበት የእብሪት ጦርነት መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ጦር ግንባር ማቅናታቸውም ኢትዮጵያን አብዝተው መውደዳቸውንና ለገቡት ቃልም መታመናቸውን ያሳያል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለአገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ" በማለት ያቀረቡትንም ጥሪ ሁሉም ሊቀበለው ይገባል ብለዋል።
ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አለመቀበል ማለት ኢትዮጵያዊነትን መዘንጋት፣ መካድ ነው፤ ከከሃዲዎች ጋርም መወገን ነው ሲሉም አርቲስት ደበበ እሸቱ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ አሁን የተጋረጠባትን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ የጥበብ ሰዎችም ኅዝቡን በማንቃትና በመቀስቀስ ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን በመወጣት የዘመኑ አርበኞች መሆን አለባቸው ብለዋል።
ወደ ጦር ግንባር መሄድ የሚችለው በመሄድ አቅም የሌለው ደግሞ ለመከላከያ ሰራዊትና ለዘማች ቤተሰቦች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ደጀንነታቸውን ማሳየት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ አሁን እያካሄደች ያለው ጦርነት የመላ አፍሪካዊያን ጦርነት መሆኑን አንስተው የምዕራባውያንን ግብዝነት ለመከላከል መላው ጥቁር ሕዝብ በእኔነት ስሜት ሊመክተው ይገባል ብለዋል።