አርቲስት ታማኝ በየነ በቅርቡ ወደ አገሩ ይመለሳል - ኢዜአ አማርኛ
አርቲስት ታማኝ በየነ በቅርቡ ወደ አገሩ ይመለሳል
አዲስ አበባ ነሀሴ 16/2010 አርቲስት ታማኝ በየነ ነሐሴ 26 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ አገሩ ይመለሳል። በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው በመመለስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በተደረገው ጥሪ መሰረት ነው አርቲስት ታማኝ በየነ ለመመለስ መወሰኑ የታወቀው። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን 'የይቅርታ፣ የፍቅርና የመደመር' ጥሪ ተቀብለው በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ አገሮች እየተመለሱ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለሶሰት ቀናት በሰሜን አሜሪካ በዋሽንግተን ዲሲ፣ ሎስ አንጀለስ እና ሚኒሶታ በመገኘት ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን ማህበረሰብ አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡ በሐምሌ 2010 ዓ.ም ወደ ሰሜን አሜሪካ በመጓዝ "ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ" በሚል መርህ እዚያው ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትወልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ውጤታማና ታሪካዊ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል። በወቅቱም አርቲስት ታማኝ በየነን ጨምሮ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ በአገራቸው እየተካሄደ ያለውን የለውጥና የመደመር ጉዞ መደገፋቸውና አስተዋጽኦ ለማበርከትም በህዝብ ፊት ቃል መግባታቸው አይዘነጋም። አርቲስት ታማኝም በወቅቱ ኢትዮጵያውያኑንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑን በማስተባበር ለአገሩ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሚሰራ መግለጹ ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና ታላላቅ ሰዎች ወደ አገራቸው እየተመለሱ ይገኛል። በቅርቡ አርቲስት ዓለምጸሀይ ወዳጆ ወደ አገሯ እንደምትመለስ ከአቀባበል ስነ ስርአት አዘጋጅ ኮሚቴው የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በዚህ የለውጥና የመደመር ጉዞ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተወዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ወደ አንድነት የመጣችበትና አቡነ መርቆሪዎስም ወደ አገራቸው መግባታቸው አይዘነጋም። ይህም የህዝቡን አንድነት የሚያጠናክርና የአገር እድገትን ያፋጥናል ተብሎ ይጠበቃል።