ጠላትን እየተናነቁ ላሉ የጸጥታ አካላት ደሜን በመለገሴ እርካታ ይሰማኛል - ኢዜአ አማርኛ
ጠላትን እየተናነቁ ላሉ የጸጥታ አካላት ደሜን በመለገሴ እርካታ ይሰማኛል
ባህር ዳር ፤ ህዳር 16/2014 (ኢዜአ) "በግንባር የህይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ጠላትን አንገት ለአንገት እየተናነቁ ላሉ የጸጥታ አካላት ደሜን በመለገሴ ውሳጣዊ እርካታም ይሰማኛል" ትላለች ተማሪዋ ።
በጤና ተቋማት የደም አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት በተደረገው ጥረት በአማራ ክልል 26ሺህ 296 ዩኒት ደም ከበጎ ፈቃደኛ ተሰብስቧል።
እሙዬ ቀሬ በባህርዳር ከተማ ጊዮን አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ናት።
ወቅቱ ከህልውና ዘመቻው ጋር ተያይዞ ብዙ ወገኖች ደም ያስፈልጋቸዋል ብላለች በሰጠችው አስተያየት።
ኢትዮጵያን ከአሸባሪው ህወሓት ለመታደግ በጦር ግንባር እየተፋለሙ የሚገኙ የፀጥታ አካላት በደም እጥረት ምከንያት ህይወታቸውን እንዳያጡ ደም መለገሷን ትናገራለች።
"በግንባር የህይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ጠላትን አንገት ለአንገት እየተናነቁ ላሉ የጸጥታ አካላት ደሜን በመለገሴ ውሳጣዊ እርካታም ይሰማኛል" ብላለች ተማሪ እሙዬ።
ወዲያው መልሶ ሊተካ የሚችለውን ደም በመለገስ ዳግም የማትገኘውን ህይወት ከመታደግ በላይ የሚያስደስት ነገር የሌለ በመሆኑ ሁሉም ሰው ለሠራዊቱ ደም የመለገስ ሃላፊነቱን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፋለች።
በዚሁ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ናትናኤል አማረ፤ "ወቅቱ ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ በግንባር ለተሰለፈው የፀጥታ ኃይል ደጀን በመሆን ደም የምንለግስበት ጊዜ ነው" ሲል የተማሪ እሙዬ ሀሳብን ያጠናክራል።
"ደም በመለገስም የጀግኖችን ውድ ህይወት ልንታደግ ይገባል" ያለው ተማሪ ናትናኤል፤ ህብረተሰቡ ስንቅ ከማዘጋጀት ጎን ለጎን ለሠራዊቱ ደሙን በመለገስ ምሳሌነቱን ማጠናከር እንዳለበት አመልክቷል።
"ደም ስለግስ የአሁኑ ለአምስተኛ ጊዜ ነው'' ያለው ተማሪው ፣ በቀጣይም የጤና ችግር እስካልገጠመው ድረስ በየሶስት ወሩ ደም በመለገስ የሠራዊቱ ደጀን ለመሆን ቃል ገብቷል።
ደም በመለገስ ከጠላት ጋር እየተዋደቁ የሚገኙ የፀጥታ አካላትን ህይወት በመታደግ ሁላችንም የዜግነት ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል ሲልም ተማሪው ተናግሯል።
"በምንሰጠው ደም ህይወትን ከመታደግ በላይ የሚያረካ ነገር የለም" ያሉት ደግሞ በጊዮን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የባዮሎጂ መምህር እስጢፋኖስ ታረቀኝ ናቸው።
"በተለይ በአሁኑ ወቅት ከህልውና ዘመቻው ጋር ተያይዞ ደም መለገስ ይበልጥ አስፈላጊ በመሆኑ ሁላችንም በእዚህ በጎ ተግባር ልንሳተፍ ይገባል" ብለዋል።
ከባህር ዳር ደም ባንክ የመጡት የጤና ባለሙያ ሲስተር ገነት አስፋው በበኩላቸው፤ ''አሁን ላይ ህብረተሰቡ የደም አስፈላጊነትን ተረድቶ በንቅናቄ ደም እየለገሰ ይገኛል'' ብለዋል።
በጊዮን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአንድ ሳምንት በተደረገው የደም ማሰባሰብ ዘመቻ 1ሺህ ተማሪዎች ደም መለገሳቸውን ገልጸዋል።
ሲስተር ገነት እንዳሉት፤ ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ እስካሁን በተከናወነው የደም ልገሳ መርሃግብር ደም ባንኩ ከ11 ሺህ ዩኒት ደም በላይ በመሰብሰቡ የአቅርቦት እጥረት አላጋጠመም።
በክልሉ ጤና ቢሮ የደም ባንክ አስተባባሪ አቶ አንዳርጌ አጥናፉ፤ ከህልውና ዘመቻው ጋር ተያይዞ ሁሉም ደም በመለገስ ህይወትን ለመታደግ እየተረባረበ መሆኑን አስታውቀዋል።
በክልሉ ስድስት የደም ባንኮች እጥረት እንዳይኖር በሙሉ አቅም አገልግሎት እየተሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ በአሁኑ ወቅት ደም የመለገስ ልምዱ እያደገ በመምጣቱ ባለፉት አራት ወራት ብቻ በክልሉ በተከናወነው ደም የማሰባሰብ ዘመቻ 26 ሺህ 296 ዩኒት ደም ተሰብስቦ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑንም አቶ አንዳርጌ አስታውቀዋል።
"የተጀመረው የደም ማሰባሰብ ሥራ በቀጣይም የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችን ቁጥር በማሳደግ የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል " ነው ያለው።