ቀጥታ፡

በካሊፎርኒያ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት በ5 ሠዓታት ያሰባሰቡትን 11 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ አበረከቱ

ህዳር 16/2014 (ኢዜአ) በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት በ5 ሠዓታት ውስጥ ያሰባሰቡትን 11 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ለአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስረክበዋል።

የድጋፉ አስተባባሪ አቶ ምኒልክ አንዳርጌ የተሰባሰበውን 10 ሚሊዮን 810 ሺህ 919 ብር ለኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስረክበዋል።

ገንዘቡ አሸባሪው ህወሓትና ግብረ አበሮቹ በከፈቱት ጦርነት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች እንደሆነ ገልጸዋል።

አቶ ምኒልክ ዳያስፖራው አገሩንና ወገኑን ለመርዳት በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ተናግረዋል።

በውጭ አገራት የሚኖሩ በሃሳብ ግን አገራቸው ውስጥ ያሉ፤ ስለ አገራቸውና ወገናቸው የሚቆረቆሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን ገልጸዋል።

አገር የገጠማትን ፈተና በአንድነት መንፈስ መወጣት እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ ያሲን በበኩላቸው ኢትዮጵያ የገጠማትን የእጅ አዙር ጦርነት ለማሸነፍ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በትብብር መንፈስ መቆም አለብን ብለዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው እያደረጉት ላለው ድጋፍ አመስግነው ድጋፉ ኮሚሽኑ በዘረጋው አሰራር ለተፈናቀሉ ወገኖች እንደሚደርስ አረጋግጠዋል።

የተሰበሰበው ድጋፍ በተለይም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ለሚገኙ ሴቶች፣ ሕፃናትና አቅመ ደካሞች ቅድሚያ የሚደርስበትን መንገድ በመፍጠር ግልፅነት ባለው መልኩ ተደራሽ ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም