የውጭ አገራት ዜጎች ከኢትዮጵያውያን ጎን በመሆን በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ተገቢ ያልሆነ ጫና እያወገዙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ አገራት ዜጎች ከኢትዮጵያውያን ጎን በመሆን በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ተገቢ ያልሆነ ጫና እያወገዙ ነው
አዲስ አበባ፣ ህዳር 16/2014 (ኢዜአ) አፍሪካዊያን እና የሌሎች አህጉራት ዜጎች በኢትዮጵያ ያለውን ተጨባጭ እውነታ በመረዳት፤ለኢትዮጵያ ድጋፋቸውን እየገለጹ ነው ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጠ ሲሆን የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ተገቢ ያልሆነ ጫና እና ጣልቃ ገብነት በተለያዩ አጋጣሚዎች እያወገዙት መሆኑን ገልጿል።
ሚኒስትር ዴኤታው ከበደ ዴሲሳ እንደተናገሩት ባለፉት ሳምንታት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባደረጉት ሰልፍ ከመንግስት ጎን መሆናቸውን አሳይተዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩት ኢትዮጵያውን ከ27 ሀገራት በላይ ባደረጉት ሰልፍ የውጭ ጣልቃ ገብነት፤ተገቢ ያልሆነ ጫና እና ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ የሚድያ ተቋማትን ማውገዛቸውን አንስተዋል።
አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንዲያከብሩም ሰልፈኞቹ መጠየቃቸውን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያውያኑ ከድጋፍ ሰልፉ በተጨማሪ አሸባሪው የህወሃት ቡድን በወረራቸው የአማራ እና አፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ዜጎች የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰባቸውንም ነው የገለጹት።
ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ወደ ሀገር በመላክ ለሀገራቸው ያላቸውን አለኝታነት ማሳየታቸውንም አክለዋል።
የአሜሪካ መንግስት ኤምባሲ የጸጥታ ስጋት አለ በሚል ዜጎቹ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ በተደጋጋሚ የሚያሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል ።
አዲስ አበባ ከተማ እንደወትሮው የጸጥታ ችግር የሌለባት፤ ሰላማዊ እና የተረጋጋ ሁኔታ ላይ መሆኗን ገልጸው፤ኤምባሲው ከአሳሳች ድርጊቱ እንዲቆጠብ አሳስበዋል።
ኤምባሲው በከተማ የጸጥታ ችግር እንዳለ በማስመሰል የሚነዛው መረጃ ዜጎችን ለማሸበር የሚደረግ ጥረት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ የሚደረጉ ጫናዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያን በሁሉም አቅጣጫ ለሀገር ሰላም የሚያደርጉትን ስራ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
የአሸባሪውን ቡድን ተልዕኮ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ጨምሮ ሌሎች አካላት መኖራቸውንም ገልጸዋል።
ሀገርን የማፍረስ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ለስንዴ ወይም ተያያዥ ድጋፎች ተብሎ የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነት እና ሉዓላዊነት አይደፈርም ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ዜጎች የጠላትን እኩይ ተልዕኮ ለማክሸፍ የሚያድርጉት ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪ አስተላልፈዋል።