ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መሪዎች ግንባር የዘመቱበት የታሪክ አጋጣሚ ሁሉ ሰራዊቱ ድል ያስመዘግባል

አዲስ አበባ ህዳር 16/2014  የኢትዮጵያ መሪዎች ወደ ግንባር በዘመቱበት የታሪክ አጋጣሚ ሁሉ የሰራዊቱ የውጊያ ሞራል ይጨምራል፤ ደጀኑም ህዝብ ይነሳሳል፤ ድልም ይመዘገባል ሲሉ የኮንጎ ሰላም አስከባሪ ጦር አባል የነበሩት ብርጋዴር ጀኔራል ካሳ ወልደሰማዕት ተናገሩ።

በ1949 ዓ.ም የኬንያ ነጻነት ታጋዮች የማኦ ማኦ ንቅናቄ ሁለት አባላትን ጨምሮ ከጀኔራል ውንጌትና ከሐረር መድሀኒያለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች  ተመልምለው ወደ ጦር ሰራዊት ከተቀላቀሉ 58 ካዴቶች መካከል አንዱ ናቸው-ብርጋዴር ጀኔራል ካሳ ወልደሰማዕት።

በታሪካዊቷ ኢሉባቦሯ ጎሬ የተወለዱት የጦር መኮንኑ በቀድሞው የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት የ17ኛ ኮርስ ምሩቅ ናቸው።

ብርጋዴር ጀኔራል ካሳ በቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ውስጥም ለ34 ዓመታት አገራቸውን አገልግለዋል።

በአገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የማስጠበቅ ዘመቻዎች በጀኔራል ከበደ ገብሬ አዛዥነት በተመራውና ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ17 አገራት ከተውጣጣው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጦር ውስጥ በኢትዮጵያ ወገን በክብር ዘበኛ የጠቅል ሻለቃ ጦር ዘማቾችም አንዱ ናቸው።

በአሜሪካው ፎርቲ ሲ ኦክሎሀማ በመድፈኛና የተመሪ ሚሳኤልት ትምህርት ቤትን ጨምሮ በአሜሪካና በሩስያ ወታደራዊና ሌሎች ትምህርቶችን የቀሰሙ ሲሆን በአሜሪካ አገር ሁዊስተን በትራንስፖርት ማኔጅመንትም ተምረዋል።

በቀድሞ ሰራዊት በሰሜን ኢትዮጵያ ከነበረው 2ኛ ክፍለ ጦር እስከ ሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት በ10ኛ እና 34ኛ ሻለቃ፣ በ6ኛ ብርጌድ፣ በ14ኛ እና በ16ኛ ክፍለ ጦር እና በሌሎች ኮሮች ከእግረኛ ተዋጊነት እስከ ኮር አዛዥነት፣ በመድፈኛ መኮንንነት የሰሩ ሲሆን በምድር ጦር በሎጀስቲክስ ክፍል በተለያዩ ሃላፊነቶች አገልግለዋል።

በ1969 ዜያድባሬ ኢትዮጵያን ለመውረር ሲመጣ ወረራውን ለመቀልበስ 'ፕሮጀክት ምስክር' የተሰኘው ኮሚቴ ውስጥ ሲዋቀር በተለይም በታጠቅ በሰለጠነው የሚሊሻ ሰራዊት ስምሪትና በከባድ መሳሪያ አሰልጣኝነት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

የደርግ መንግስት ሲገረሰስ የሕወሃት ስርዓት የኢትዮጵያን ጦር ሰራዊት ሲበተን ብርጋዴር ጀኔራል ካሳም ለ13 ዓመታት የግፍ እስር ገጥሟቸዋል።

እኝህ ታላቅ ያአገር ባለውለታ ጀግና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በውጭ አገራት ድጋፍ እስከ አፍንጭዋ የታጠቀችው ሶማሊያ ኢትዮጵያን ስትወረር አብዮት ላይ የነበረችው ኢትዮጵያ የተደራጀ ትጥቅ አልነበራትም።

አሜሪካን ጨምሮ ድጋፍ የተጠየቁ አጋሮችም ድጋፋቸውን እንዳልሰጡ ይልቁኑም በከፍተኛ የአገር ሀብት ክፍያ የተፈጸመባቸው የጦር መሳሪያዎችም ላለመስጠት ስለመከልከላቸው አስታውሰዋል።

በወቅቱ አገራዊ ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር ግን ወረራውን መቀልበስና የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ማስጠበቅ ስለመቻሉ ያነሳሉ።

አገር ሲደፈር ኢትዮጵያዊያን በክተት እየተመሙ የአገር ሕልውናን ማስጠበቅ ነባር ልማዳቸው እንደሆነ የአድዋን፣ የማይጨውና የሶማሊያን ወረራ ለአብነት አንስተዋል።

የወቅቱ የኢትዮጵያን ሕልውናን የማረጋገጥ ዘመቻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ግንባር መዝመታቸው ከነባር የመሪዎች ዕሴት የተቀዳ እርምጃ መሆኑን ዳግማዊ አጼ ምኒልክን፤ አጼ ሃይለስላሴና ፕሬዝዳንት መንግስቱ ሃይለማርያምን ለአብነት በማንሳት ያስረዳሉ።

የጠቅላይ ሚኒሰትሩና የአመራሮች በግንባር መሰለፍም በግንባር ለሚዋደቀው ጦርም ሆነ ለደጀኑ ህዝብ ትልቅ ሞራልና መነሳሳትን የሚፈጥር ስለመሆኑ አንስተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎም ህዝቡ ቀፎው አንደተነካበት ንብ ወደ ግንባር እየተመመ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም በክተት የመጣው የታጠቅ የሚለሻ ጦር ትልቅ ጀብዱ በመፈጸም ነጻነትና ሉዓላዊነት እንዳስገኙ ገልጸው፤ ዛሬም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚሰራው የሽብርተኛ ሕወሃት ቡድን ወረራ ለመቀልበስ የህዝብ አንድነት ያስፈልጋል ብለዋል።

አሸባሪው ህውሃ ባልታሰበ አኳኋን የሰሜን ዕዝን ከጀርባ በጭካኔ በመውጋት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያዊያን ይህን ቡድን በትብብር መደምሰስ ይገባል ብለዋል።

ይህ ቡድን በአንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት ድጋፍ እየተደረገለት በመሆኑ ኢትዮጵያ ከጁንታ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ሃይሎች ጋር የምትዋጋበት የሕልውና ዘመቻ መሆኑን ነው ያነሱት።

የሶማሊያ ወረራን መቀልበስ የተቻለው ሲቪሉም፣ ወደ ጦር ግንባር እየገባ ተዋግቶ፣ ደጀኑ ህዝብ ለሰራዊቱ ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮና በአገራዊ ስሜት ተነስቶ በመሆኑ፤ ዛሬም ይህን መድገም ይገባል ነው ያሉት።

አሸባሪው ቡድን ህጻናትን በሀሺሽ በማደንዘዝ ወደ ጦር ሜዳ በማስገባት ከማስጨረስ በስተቀር ዳግም ወደ አዲስ አበባ መምጣት የማይታሰብ መሆኑን ተናግረዋል።

ወያኔ ዋናው የሚታወቅበት የራሱን ሰዎች በህዝብ መሃል በማስረግ ህዝብን ማሸበር ብሎም ከጀርባ ማስወጋት መሆኑን ገልጸዋል።

በአስካአሁኑም የአሸባሪው አካሄድ ይሄ መስተዋሉን አስታውሰው፤ በየከተማው ለ27 ዓመታት በጦር ሰራዊቱ ብቻ መያዝ ያለባቸው መሳሪያዎችን ሲያስታጥቅ የከረመ ቡድን በመሆኑ ፍተሻው ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

በአዲስ አበባ የተጀመረውን የጥንቃቄ እርምጃ አድንቀው፤ ይህ በሌሎችም አካባቢዎች የተሰገሰጉትን መመንጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በከሃዲዎች ፈፅሞ አትፈርስም ያሉት ብርጋዴር ጀኔራል ካሳ፤ ለህልውናዋ በጋራ እንቁም ብለዋል።

የቀድሞ ጦር ሰራዊትም ለአገር ህልውናው የተደረገለት ጥሪ መልካም እድል መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም