ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅና ስራ ባልደረቦቻቸው ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅና ስራ ባልደረቦቻቸው ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለጹ
አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ዲፕ ካማራና የስራ ባልደረቦቻቸው ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት በኢትዮጵያ በሚገኘው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅና ሁለት የስራ ባልደረቦቻቸው ላይ በተፈመው አሰቃቂ ግድያ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግስት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው ተናግረዋል። ለሟቾቹ ቤተሰቦች እና ለመላው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሰራተኞች መፅናናትን ተመኝተዋል። መንግስት ግድያውን የፈጸሙትን አካላት እያጣራ መሆኑንና አጥፊዎችን ለህግ እንደሚያቀርብም ገልጸዋል። የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን አደኣ በርጋ ወረዳ የሚገኝ ነው። ከሶስት ዓመት በፊት ስራውን የጀመረው ፋብሪካው ሲሚንቶ የማምረት አቅሙ በኢትዮጵያ ትልቁ የሚባል ነው። በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን አደኣ በርጋ ወረዳ በሚገኘው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ዲፕ ካማራና ሁለት የስራ ባልደረቦቻቸው ትናንት ባልታወቁ የታጠቁ ሰዎች በተፈፀመባቸው ጥቃት ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው። በአሁኑ ወቅት መንግስት ግድያ የፈጸሙ አካላትን ለመያዝ ጥብቅ ክትትል በማድረግ ላይ እንደሆነና ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ በሚደረገው ጥረትም ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ መጠየቁም ይታወሳል።