ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አፈጻጸም ከዕቅዱ ከ50 በመቶ በታች ነው

አዲስ አበባ ነሀሴ 16/2010 የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኤሌክትሪክ መቆራረጥና የውጭ ምንዛሬ እጥረት የተነሳ ከዕቅድ በታች መሥራቱን አስታወቀ። ኢንስቲትዩቱ የበጀት ዓመቱን የሥራ አፈጻጸም ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ውይይት አካሂዷል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከጨርቃ ጨርቅና ስፌት ኢንዱስትሪ ምርቶች የውጭ ንግድ 239 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማግኘት ቢያቅድም የተገኘው ገቢ 109 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው። ይህም የዕቅዱን 46 በመቶ ሲሆን ከኢንዱስትሪ ፓርክ ውጭ ያሉ የውጭ አገር ባለሀብቶች፣ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች፣ ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ከቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ እና ከኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ መጠን ከ40 በመቶ በታች ነው። የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ  ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ከዕቅድ በታች ለተመዘገበው ውጤት የኤሌክትሪክ መቆራረጥና ለፋብሪካዎች ግብዓት ከውጭ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ሆኗል። እንዲሁም በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የነበረው አለመረጋጋት በባለሀብቶች ላይ ያሳደረው ጫና ለዘርፉ የዕቅድ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰው የፋብሪካዎች የአሰራር ድክመትና አቅምን አሟጦ አለመጠቀም ሌላው ምክንያት እንደነበረ ተናግረዋል። በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት የ2011 በጀት ዓመት ስኬታማ የዕቅድ አፈጻጸም ለማሰመዝገብ መታቀዱን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም