ቀጥታ፡

''ኢትዮጵያዊነትን በተግባር የገለጹና የአባቶቻችን ጀግንነት በዓይናችን ያሳዩ መሪ !"

ሚዛን አማን ኅዳር 15/2014 (ኢዜአ''ኢትዮጵያዊነትን በተግባር የገለጹና የአባቶቻችን ጀግንነት በዓይናችን ያሳዩ መሪ !"በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን በአድናቆትና በፍቅር የገለጻቸው የሚዛን አማብ ከተማው ወጣት ነው።
ወጣቱ ልዑልሰገድ ይመር ይባላል።በአዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በቀድሞው ደቡብ ክልል የቤንች ሸኮ ዞን ርዕሰ ከተማ ይኖራል።

በሀገሪቱ 11ኛ ሆኖ ትናንት በይፋ በተመሰረተው ክልል የሚኖረው ይሄ ወጣት ኢትዮጵያን በደንብ የሚያውቅበት ዘመን ላይ ነው የተፈጠረው።

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በሚፈቅደው ፌዴራላዊ አወቃቌ ራስን በራስ የሚያስተዳድርበት ጊዜ ላይ አድርሶታል።

ለዜጎቿ የምትመች ኢትዮጵያ ስትገነባና ከለውጡ ወዲህ ሁለተኛው ክልል ሲመሰረት ለማየትም በቅቷል።

በሕዝብ ይሁንታ መንግሥት መስርቶ ሀገር የሚያስተዳድረውን አካል ''አሃዳዊ'' ነው ብለው የሚያላዝነውና ሀገር ለማፈራረስ የተነሳውን አሸባሪውን ህወሓት ጉድም ሰምቷል።

እናም ልዑል ሰገድ በአዲሱ ክልል ምስረታ ዋዜማ የሰማው ዜና የኢትዮጵያን ታሪክ አስታውሶታል።

የቀደምት መሪዎችን ታሪክ የሚያድሱ መሪ በዚህ ዘመን አገሩ እንዳላት አረጋገጠ-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን። 

"'ዝመቱ' ከማለት ተሻግረው ራሳቸው በመዝመት 'እዚያው እንገናኝ' የሚል ጥሪ አስተላልፈው ወደ ግንባር መሄዳቸው ኢትዮጵያ እንደ ጥንቱ ጀግናና ኩሩ መሪ እንዳላት አሳይተውናል" በማለትም አድናቆቱን ገልጿቸዋል።

''ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘምተው እንቅልፍ የሚተኛ ኢትዮጵያዊ መኖር የለበትም'' የሚለው ልዑል ሰገድ፣

ፈለጋቸውን ተከትሎ ጥሪያቸውንም አክብሮ የሕልውናውን ዘመቻ ለመቀላቀል ተዘጋጅቻያለሁ ብሏል።

ወደ ግንባር የማይዘምተው ሕዝብ ለመከላከያ ሠራዊት ስንቅ በማዘጋጀት፣ ደም በመለገስ እንዲሁም የዘማች ቤተሰቦችን በመደገፍ ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣም ጠይቋል።

ወጣት ማስረሻ መንገሻም ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ግንባር መዝመታቸው ''ሀገር የመምራት ኃላፊነት ጥግ እስከ መስዋዕትነት መሆኑን አሳይተውናል''ይላል።

ለወጣቱ ትውልድም ህያው ታሪክ ጽፈው እንዳስነበቡ ይቆጠራል ብሏል።

ለመዝመት ዝግጁነቱን ያረጋገጠው ማስረሻ፣ ኢትዮጵያውያን ሁለት ነገሮችን እንፈጽም ይላል፦'' በግንባር ያሉትን በመቀላቀልም ሆነ ስንቅ በማቀበል።"

ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት ሽመልስ ስንታየሁ ነው። ዶክተር ዐቢይ ወደ ግንባር መዝመታቸውና ለዜጎች ያቀረቡት ጥሪ መከላከያ ሠራዊት ለመቀላቀል አነሳስቶኛል ብሏል።

''የሀገር ፍቅርን ከቃላት ባለፈ በተግባር ለማሳየት ጊዜው አሁን ነው'' ሲልም አክሏል።

አሸባሪውና ወራሪው ህወሓት ሕዝቡ በመረጠው መንግሥት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በቆፈረው ጉድጓድ ራሱን መቅበር የዘመኑ ወጣቶች ግዴታ መሆኑን ገልጿል።

"እኛ እያለን የኢትዮጵያ ታሪክ አይበላሽም፤ የተማረ ያልተማረ ሳንል የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ ቆርጠን ተነስተናል" ሲልም ሽመልስ የራሱንና የዕድሜ እኩዮቹን አስተያየት አንጸባርቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም